መግቢያ. 1.1 ኢትዮጵያ የብሔራዊ የክፍያ ሥርዓቱን ደህንነት፣ አስተማማኝነትና ቅልጥፍና ለማረጋገጥ እንዲቻል ሥርዓቱ ስለሚቋቋምበት፣ ሰለሚተዳደርበት፣ አሠራሩ ስለሚመራበት እንዲሁም አስፈላጊዉ ቁጥጥርና ክትትል ስለሚካሄድበት ሁኔታ በብሔራዊ የክፍያ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 718/2003 አዉጥታ ሥራ ላይ አዉላለች፡፡ 1.2 አዋጁን መሠረት በማድረግ “አር.ቲ.ጂ.ኤስ.” የተሰኘዉን ትልልቅና ወሳኝ ክፍያዎችን የሚያሳልጠዉንና “ኤ.ሲኤች.” በመባል የሚታወቀዉን አዉቶሜትድ የቼክ ማጣሪያ ሥርዓት አጣምሮ የያዘዉ “ኢ.ኤ.ቲ.ኤስ.” የተባለዉ የኢትዮጵያ አዉቶሜትድ የገንዘብ ማስተላለፊያ ሥርዓት እ.ኤ.አ. በ2011 በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተግባራዊ መደረጉን ተከትሎ ትልልቅና ወሳኝ ክፍያዎችን በቅፅበት ከአንድ ጫፍ ወደ ሌላኛዉ መፈፀም ተችሏል፡፡ በዚህም ስርዓት አማካይነት በቀን በአማካይ መጠናቸዉ ከ12 ቢሊዮን ብር በላይ የሆነ ከ9,500 በላይ ግብይቶች ይተላለፉባቸዋል፡፡ ይህም የክፍያ ሥርዓቱን ቀደም ሲል ከነበረበት ሁኔታ ከመሠረቱ የቀየረ ነዉ ማለት ይቻላል፡፡ ከዚህም ሌላ እንደ ደመወዝ ያሉትን ብዛት ያላቸዉን ክፍያዎች በባንክ ሂሳብ በኩል በአንድ ጊዜ ለመክፈል የሚያስችለዉ “ክሬዲት ትራንስፈር” አገልግሎት በቅርቡ ተግባራዊ መደረጉ ይታወቃል፡፡ 1.3 ከዚሁ ጎን የክፍያ መሠረተ ልማት በማቅረብ የክፍያ ሥርዓቱ እርስ በርሱ የሚናበብና የሚገናኝ በማድረግ ጥቃቅን ክፍያዎችን፣ የአገር ዉስጥ ጨምሮ የካርድ ክፍያን፣ የሞባይልንና የክፍያ ነቁጥን፣ ብሔራዊ ጌትዌይንና ሌሎችንም አገልግሎቶች ከማሳለጥ አኳያ የአስቻይ ሚና እንዲጫወት ኢትስዊች እንደ ብሔራዊ ስዊች እኤአ በ2011 ተቋቁሞ በ2016 ሥራ መጀመሩ ይታወቃል፡፡ 1.4 እስካሁን ኩባንያዉ ኤቲ.ኤም.ን፣ የክፍያ ነቁጥን እና ከግለሰብ ወደ ግለሰብ በሞባይል አማካይነት የሚደረገዉን የገንዘብ ዝዉዉር ተናባቢ እንዲሆን ያደረገ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በቀን በአማካይ ዋጋቸዉ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ ከ60,000 በላይ ግብይቶች በዚሁ ስርዓት አማካይነት ይተላለፉበታል፡፡ በተመሳሳይ ሌሎቹን መተግበሪያዎችንና የክፍያ መሳሪያዎችን ተናባቢ ለማድረግ የጀመረዉን ሥራ ኩባንያዉ አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ 1.5 ከዚህም ሌላ በአዋጁ መሠረት ሶስት መመሪያዎች ማለትም፡- ‹የክፍያ መፈፀሚያ ሰነድ አዉጪ›፣ ‹የክፍያ ሥርዓት ኦፕሬተር› እና ‹በወኪል መሥራት› የተሰኙ መመሪያዎች ወጥተዉ ተግባራዊ ተደርገዋል፡፡ እነዚህን መመሪያዎች ተከትሎ እስካሁን ኢትዮ ቴሌኮም የክፍያ መሳሪያ አዉጪ ፈቃድ በመዉሰድ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት መስጠት የጀመረ ሲሆን ሌሎች ሶስት ኩባንያዎችም የክፍያ ሥርዓት ኦፕሬተር ፈቃድ ወስደዉ ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ ሌሎቹም በመግባት ላይ ናቸዉ፡፡ 1.6 ከብሔራዊ የክፍያ ስርዓት አዋጅ በተጨማሪ የፋይናንስ ተቋማትን አዋጆች ጭምር እንዲከለሱ በማድረግ በመንግሥት በኩል ዲጂታል የፋይናንስ አገልግሎት ማለትም በዲጂታል ዘዴ የክፍያ፣ የሃዋላ እና የመድን አገልግሎት አቅራቢዎች እንደ ፋይናንስ ተቋማት እንዲቆጠሩ የተደረገዉ የሪፎርም ሥራ ለዘርፉ ዕድገት በወሳኝ መልኩ አስተዋፅዖ አድርጓል ለማለት ይቻላል፡፡ 1.7 በዚህም መሠረት እስካሁን 6,793 ኤ.ቲ.ኤም ተርሚናል፣ 11,714 የክፍያ ነቁጥ ማሽን ፣ 15.5 ሚሊዮን የሞባይል ባንኪንግ ደንበኞች፣ 3.9 ሚሊዮን የኢንተርኔት ባንኪንግ ተጠቃሚዎች፣ 28.76 ሚሊዮን ዴቢት ካርዶች፣ 35.5 ሚሊዮን የሞባይል ገንዘብ ተጠቃሚዎች አና 137,378 ወኪሎች በሥራ ላይ መሆናቸዉን እ.ኤ.አ የማርች 2022 መረጃ ያመለክታል፡፡ የግብይት ሂሳብ ቁጥርም በከፍተኛ ደረጃ አድጎ 130.4 ሚሊዮን ደርሷል፡፡ 1.8 ምንም እንኳን አገራችን ከላይ እንደተጠቀሰዉ ዘመናዊ የክፍያ ሥርዓትንና ዲጂታል የፋይናንስ አገልግሎትን በተመለከተ አስደማሚ ጅምር ላይ ብትሆንም እጅግ ዘግይታ ከመጀመሯ አንፃር የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ (ምናልባትም ከ95 በመቶ በላይ) ጥሬ ገንዘብ የሚጠቀም ሲሆን 45 በመቶ የደረሰዉ የፋይናንስ አካታችነት ምጣኔም ከጎረቤቶቻችንና ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገሮች አንፃር ሲታይ በጣም ዝቅተኛ የሚባል ነዉ፡፡ የፋይናንስ አገልግሎት በተለይም የብድር አገልግሎት ከ5 ሚሊዮን ብዙም ያልዘለለ ሆኖ ተደራሽነቱም አዲስ አበባን ጨምሮ በጥቂት ትልልቅ ከተሞችና ተበዳሪዎች አካባቢ ዉስን ሆኖ ይገኛል፡፡ 1.9 በሌላ በኩል ምንም እንኳን ከሁለት ዓመታት በፊት የዉጭ አገር ዜግነት ያላቸዉ ትዉልደ አትዮጵያውያን በፋይናንስ ዘርፍ ሙአለ ንዋያቸዉን እንዲያፈስሱ የተፈቀደላቸ...