• Sunday, 29 March 2015 11:00
ስምምነቱ ሁሉንም ተጠቃሚ ያደረገ ነው፡- ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም
• Sunday, 29 March 2015 11:00
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን የፈረሙት የመርሆዎች ስምምነት ሁሉንም ተጠቃሚ ያደረገ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ገለጹ፡፡
ዶ/ር ቴድሮስ ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት ሶስቱ ሀገራት በካርቱም የፈረሙት ስምምነት መሠረቱ ዓለም አቀፍ መርሆዎች ናቸው፡፡
አስር ነጥቦች ያሉት ስምምነት ትብብርን፣ አካባቢያዊ ትስስርና ዘላቂ ልማትን፣ ጉልህ ጉዳት ያለማድረስን፣ ፍትሐዊና ተገቢ የውሃ አጠቃቀምንና ግድቡን የመሙላትና የግድቡ ስራ ፖሊሲ መርህን አካቷል፡፡
ዶ/ር ቴድሮስ እንዳሉት ሀገራቱ የታላቁ ህዳሴ ግድብን በተመለከተና በአባይ ወንዝ ፍትሐዊና ምክንያታዊ አጠቃቀም ላይ ያካሄዱት ድርድር ሁሉንም ተጠቃሚ ያደረገ ነው፡፡
ድርድሩ አድካሚ የነበረ ቢሆንም በመርሆቹ ላይ መስማማትና መቀራረብ መፈጠሩ ስምምነቱ እንዲፈረም ማስቻሉን የገለጹት ሚንስትሩ ስምምነቱ ፍትሐዊ የውሃ አጠቃቀም እንዲኖር ስለሚያደርግ ለዚህ ተፈጻሚነት ሁሉም መንቀሳቀስ አለበት ብለዋል፡፡
የግብጽ መንግስት አባይ ወንዝ አጠቃቀምን በተመለከተ ያራምዳቸው የነበሩ ስትራቴጂዎችን በማሻሻል ወደ ድርድር መምጣቱ ለስምምነቱ መፈረም አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡
ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን ድንበር ተሻጋሪ የውሃ ሃብታቸውን የመጠቀም ፍላጎታቸው ማደጉና ለህዝቦቻቸውም ህይወትና ልማት ምንጭ በመሆኑ ስምምነቱ ለጋራ ተጠቃሚነትነታቸው መሠረት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን መሪዎች የታለቁ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ የመርሆዎች ስምምነት በሱዳን ባለፈው ሰኞ መፈረማቸው ይታወሳል፡፡
ሪፖርተር፡- ብርቱካን ሐረገወይን