Contract
መጋቢት30 ቀን 2014 ዓ.ም የኮ/መ/ቁ. 294960
ልደታ ምድብ 7ኛ ፍ/ብሔር ችሎት
ዳኛ፡ አሳሂብ ብዙነህ
ከሳሽ፡ አቶ አላማር ደበላ ሺፋ - ቀረቡ
ተከሳሽ፡ 1. አቶ መሐመድ ሸምሱ አወል - ጠበቃ ተስፋዬ ላሎቶ ቀረቡ
2. አቶ ገመቺስ ጋሻው ኬሶ
መዝገቡ ለዛሬ ቀጠሮ የያዘው መርምሮ ፍርድ ለመስጠት ሲሆን ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡
ፍ ር ድ
ለፍርዱ መነሻ የሆነው ከሳሽ ሐምሌ 26 ቀን 2013 ዓ.ም ጽፈው ያቀረቡት የክስ አቤቱታ ሲሆን ይዘቱም በአጭሩ 1ኛ ተከሳሽ በስማቸው ተመዝግቦ የሚገኝ እና የካርታ ቁጥሩ 02/263/0017225/00 የሆነ በቀድሞው ወረዳ 23 ቀበሌ 14 በአሁኑ ወረዳ 2 ክልል ይዞታ ያላቸው ሲሆን 1ኛ ተከሳሽ ይህንኑ ይዞታ በማስመልከት በውክልና ቁጥር 14/0002061/1/2012 በቀን 14/12/2012 ዓ.ም ለ2ኛ ተከሳሽ በን/ስ/ላፍቶ ክ/ከተማ ወረዳ 02 ክልል ውስጥ የሚገኘውን የግል ይዞታቸውን ለመሸጥ፣ ለመለወጥ እንዲሁም የሽያጩን ገንዘብ ለመቀበል የሚያስችል ውክልና የሰጡ ሲሆን 2ኛ ተከሳሽ ይህንኑ ውክልና ተጠቅመው በ1ኛ ተከሳሽ ስም ተመዝግቦ የሚገኘውን የመኖሪያ ቤት ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም በተደረገ የሽያጭ ውል ለከሳሽ በብር 7,650,000.00/ሰባት ሚሊዮን ስድስት መቶ ሀምሳ ሺህ/ በሽያጭ አስተላልፈዋል፡፡ በእለቱም በውሉ ደረሰኝነት ከሽያጭ ገንዘቡ ላይ ብር 650,000.00/ስድስት መቶ ሀምሳ ሺህ/ ቀብድ ተቀብለዋል፡፡ በከሳሽና በተከሳሾች መካከል በተደረገው የስልክ ልውውጥ ከቀሪው የሽያጭ ገንዘብ ውስጥ ብር 2,000,000.00/ሁለት ሚሊዮን/ በቀብድነት እንዲሰጣቸው ወይም እንዲላክላቸው ጠይቀው በተደረሰው ስምምነት በ2ኛ ተከሳሽ ስም
በአቢሲኒያ ባንክ መካኒሳ ቅርንጫፍ በሂሳብ ቁጥር 68126819 ሰኔ 29 ቀን 2013 ዓ.ም ከከሳሽ የሂሳብ ቁጥር 68693993 ገቢ ተደርጎላቸዋል፡፡
ከሳሽ ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም በተደረገው የቤት ሽያጭ ውል ስምምነት መሰረት ተከሳሾች ቀሪውን የሽያጭ ገንዘብ ብር 5,000,000.00/አምስት ሚሊዮን/ተቀብለው ቤቱን እና የቤቱን ሰነዶች እንዲያስረክቡን እንዲሁም የቤቱን ሽያጭ ቀሪ ገንዘብ ከመቀበላቸው በፊት በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ቀርበው የውል ግዴታቸውን እንዲወጡ በተደጋጋሚ ብጠይቃቸውም ሊፈፅሙ ፍቃደኛ ሆነው ባለመገኘታቸው ከሳሽ በጠበቃዬ በኩል ሰኔ 22 ቀን 2013 ዓ.ም ለ1ኛ ተከሳሽ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ሰጥቻለሁ፡፡
በመሆኑም ፍርድ ቤቱ ተከሳሾች ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም በተደረገው የሽያጭ ውል መነሻነት በውሉ ተመለከተውን ቤትና ይዞታ ቀሪ የሸያጭ ገንዘባቸውን ተቀብለው ቤቱን እና የቤቱን ሰነዶች ለከሳሽ እንዲያስረክቡና በሚመለከተው የአስተዳደር አካል ፊት ቀርበው የቤቱን ስመ ሀብት እንዲያዛውሩ እንዲወስንልን ተከሳሾች ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም በተደረገው የሽያጭ ውል መሰረት ለመፈፀም ፍቃደኛ ካልሆነኑ በውሉ ደረሰኝነት የወሰዱትን ብር 650,000/ስድስት መቶ ሀምሳ ሺህ/ እንዲሁም ሰኔ 29 ቀን 2013 ዓ.ም ከከሳሽ የሂሳብ ቁጥር 68693993 ወደ 2ኛ ተከሳሽ የባንክ ሂሳብ ቁጥር 68126819 ገቢ የተደረገውን ብር 2,000,000.00/ሁለት ሚሊዮን/ በአጠቃላይ ብር 2,650,000.00/ሁለት ሚሊዮን ስድስት መቶ ሀምሳ ሺህ/ ቃብድ የተቀበሉ በመሆኑ የዚህን ገንዘብ አጠፌታ ተከሳሾች ለከሳሽ እንዲከፍሉ ይወሰንልኝ በማለት ጠይቀዋል፡፡ የሰውና የሰነድ ማስረጃ ዝርዝር አያይዘው አቅርበዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ የከሳሽ የክስ አቤቱታ ከነአባሪው ለተከሳሾች እንዲደርስ እና መከላከያ መልሳቸውን በጽሁፍ አዘጋጅተው እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ተሰጥቶ ተከሳሾች በጋራ ጥቅምት 11 ቀን 2014 ዓ.ም የተፃፈ የመከላከያ መልስ ያቀረቡ ሲሆን ይዘቱም በአጭሩ ከሳሽና ተከሳሽ በሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም በፈጸምነዉ ግልጽ የሽያጭ ዉል ስምምነት መሰረት በን/ስ/ላ/ክ/ከ ወረዳ 02 ዉስጥ የሚገኘዉንና የካርታ ቁጥር 02/263/0017225/00 የቦታዉ ስፋት 460 ካ.ሜ የሆነ ይዞታ በብር 7,650,000 (ሰባት ሚሊየን ስድስት መቶ ሃምሳ ሺህ ብር) ተዋዉለን አከፋፈሉንም በተመለከተ በእለቱ ብር 650,000(ስድስት መቶ ሀምሳ ሺህ) በቀብድ በባንክ ከሳሽ የከፈለ ሲሆን ሁለተኛዉ ዙር ክፍያ በሰኔ 18 ቀን 2013 ዓ.ም(በነጋታዉ) ብር 4,000,000(አራት ሚሊየን) ከሳሽ ለመክፈልና ቀሪዉን ሶስተኛ ዙር እና የመጨረሻ ክፍያ 3,000,000ብር(ሶስት ሚሊየን ብር) እስከ ሐምሌ 02 ቀን 2013ዓ.ም ለመክፈል ከሳሽ ተስማምቶ ግዴታ መግባቱን በዉሉ ላይ
በግልጽ ተመልክቷል፡፡ ይህ ግልጽ ዉል እያለ ከሳሽ በቀብድ በባንክ ሂሳብ ካስገባዉ ብር 650,000(ስድስት መቶ ሀምሳ ሺህ) ዉጪ በዉሉ ላይ በተቀመጠዉ ሰኔ 18 ቀን 2013 ዓ.ም በዉሉ መሰረት ብር 4,000,000(አራት ሚሊየን) ማስገባት ወይም መክፈል ሲጠበቅበት ይህን ግዴታዉን ሳይወጣ በመቅረቱ ዉሉን ያፈረሰዉ ከሳሽ ራሱ እንጂ ተከሳሾች አይደለንም፡፡ ዉል በተዋዋዮች መካከል ሕግ እንደመሆኑ መጠን በዉሉ ላይ በግልጽ የተቀመጠዉን የክፍያ ጊዜ ጠብቆ ከሳሽ ማስገባት ወይም መክፈል ግዴታዉ የነበረበት ቢሆንም ከሳሽ ግን ቀብድ ከፍያለዉ በሚል በዉሉ ላይ የተቀመጠዉን ግዴታዉን ሳይወጣ ቀርቶ አሁን በዉሉ መሠረት ግዴታዉን እንደተወጣ በማስመሰል በዉሉ መሠረት እንዲፈጸም ያቀረበዉ ክስ ተቀባይነት ሊኖረዉ አይገባም፡፡ ከሳሽ በዉል ላይ በተቀመጠዉ ጊዜ ክፍያ ባለመክፈሉ የተነሳ ተከሳሾች ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም ማስጠንቀቂያ የሰጠነዉ ቢሆንም በማስጠንቀቂያዉ መሠረትም ግዴታዉን ሳይወጣ ቀርቷል፡፡ ከሳሽ በክስ አቤቱታዉ ላይ ብር 2,000,000(ሁለት ሚሊየን ብር) በቀብድነት እንዲላክላቸዉ በተደረገዉ ስምምነት በ2ኛ ተከሳሽ በአቢሲኒያ ባንክ መካኒሳ ቅርንጫፍ በሂሳብ ቁጥራቸዉ ሰኔ 29 ቀን 2013ዓ.ም ገቢ አድርጊያለሁ ቢልም በዉላችን ላይ ስለ ሁለት ሚሊየን ብር ክፍያ ጭራሹኑ የሌለ ከመሆኑም በተጨማሪ ቀደም ሲል የፈጸምነዉ በሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም የሽያጭ ውል በጽሁፍ እንደመደረጉ መጠን ይህን ዉል በሌላ ጽሁፍ ዉል ስለመተካቱ ያቀረበዉ ምንም ማስረጃ በሌለበት ከሳሽ በራሱ ጊዜ ሊያዉም ተከሳሾች ማስጠንቀቂያ ከሰጠንበት እንዲሁም በዉሉ ላይ ከተቀመጠዉ ቀናት እና የገንዘብ መጠን ዉጪ ተከሳሸ ገቢ ያደረገዉ ብር 2,000,000.00(ሁለት ሚሊየን) በምንም መልኩ በዉሉ መሠረት ከሳሽ ግዴታዉን ተወጥቷል ሊያሰኝ አይችልም፤ ይህን ብር ከሳሽ ካስገባ በኃላ በቅንነት ከዉላችን ዉጪ ያስገባዉን 2,000,000ብር(ሁለት ሚሊየን ብር) መዉሰድ ትችላለህ፤ይመለስልህ ስንለዉም ከሳሽ ፈቃደኛም አልነበረም፡፡ አሁንም ቢሆን ይህን ከሳሽ ከዉል ዉጪ ገቢ ያደረገዉን 2,000,000ብር(ሁለት ሚሊየን ብር) መዉሰድ ይችላል፡፡ በመሆኑም በሰኔ 17 ቀን 2013ዓ.ም የተጻፈዉ ዉል ያፈረሰዉና ያልፈጸመዉ ከሳሽ ራሱ በመሆኑ በፍ/ሕ/ቁጥር 1885(2) መሰረት በዉሉ መሠረት ያልተፈጸመዉ ወይም ዉሉን ያፈረሰ ከሳሽ በመሆኑ በዉል ላይ የተጠቀሰዉን ቀብድ ከሳሽ መጠየቅ ስለማይችል የተከበረዉ ፍ/ቤት የከሳሽን ክስ ዉድቅ በማድረግ ዉሳኔ እንዲሰጥልን ከሳሽ እና ተከሳሽ በሰኔ 17 ቀን 2013ዓ.ም በፈጸምነዉ ዉል ላይ የቀብድ ገንዘብ መጠኑ ብር 650,000(ስድስት መቶ ሀምሳ ሺህ) ስለመሆኑ በግልጽ በዉሉ ላይ የተጠቀሰና በባንክ ገቢ የሆነ ሲሆን ከሳሽ ከዉሉ ዉጪ ክሱን ሲያቀርብም ሆነ ዳኝነት ሲጠይቅ የቀብድ ገንዘቡ ብር 2,650,000(ሁለት ሚሊየን ስድስት መቶ ሀምሳ ሺህ) ነዉ በማለት የዚህ የገንዘብ መጠን
አጠፌታዉን እንዲከፈለዉ ዳኝነት ጠይቋል፡፡ በከሳሽና ተከሳሸ መካከል ግልጽ ዉል ባለበት እና የቀብድ ገንዘቡም መጠን በግልጽ ተቀምጦ ባለበት ከሳሽ ሆነ ብሎ የቀበድ ገንዘቡ ብር 2,650,000(ሁለት ሚሊየን ስድስት መቶ ሀምሳ ሺህ) በማለት ያቀረበዉ ክስ አግባብነት የሌለዉና የቀብድ ዉል ህግጋትን የጣሰ ነዉ፡፡ ከሳሽ በክሱ ላይ በስልክ ልዉዉጥ ከቀሪ የሽያጭ ገንዘብ በተጨማሪነት ብር 2,000,000(ሁለት ሚሊየን) በቀብድ እንዲሰጣቸዉ ወይም እንዲላክላቸዉ በተደረሰዉ ስምምነት በ2ኛ ተከሳሽ የባንክ ሂሳብ ገቢ አድርጊያለዉ ያለዉ ፈጽሞ ሀሰት ከመሆኑም በተጨማሪ ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም የተፈጸመዉ ዉል የጽሁፍ ዉል እንደመሆኑ መጠን ይህን ዉል ለመለወጥም ሆነ ለማሻሻል ወይም ተጨማሪ ዉል ለማድረግ በፍ/ሕ/ቁጥር 1722 መሠረት በጽሁፍ መደረግ እንደሚገባዉ ከተደነገገዉ የህግ ደንጋጌ አንጻርም የከሳሽ የክስ ፍሬ ነገር የሕግ ድጋፍ የለዉም፡፡ በመሆኑም የተከበረዉ ፍ/ቤት ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም በተፈጸመዉ ዉል መሠረት የቀብድ ገንዘብ መጠኑ ብር 650,000(ስድስት መቶ ሀምሳ ሺህ) እንጂ ብር 2,650,000(ሁለት ሚሊየን ስድስት መቶ ሀምሳ ሺህ) አይደለም እንዲባልልን፣ ከሳሽ በክሰ አቤቱታዉ ላይ በሰኔ 17 ቀን 2013ዓ.ም በተጸፈመ የቤት ሽያጭ ዉል መሠረት ተከሳሾች ቀሪ ገንዘባቸዉን 5,000,000ብር(አምስት ሚሊየን ብር) ተቀብለዉ ቤቱንና የቤቱን ሰነድ በህግ ሀይል ተገደዉ እንዲያስረክቡኝ እና ወደ ሚመለከተዉ መንግስታዊ አካል ቀረበዉ ስመ ሀብቱን እንዲያዛዉሩ በማለት ያቀረበዉ ክስ ከላይ በዝርዝር እንዳቀረብነዉ በዉሉ መሠረት ያልፈጸመዉና ዉሉንም በራሱ ምክንያት ያፈረሰዉ ከሳሽ ራሱ ስለሆነ ዉሉን መሠረት በማድረግ ያቀረበዉ የዳኝነት ጥያቄ አግባብነት የለዉም ተብሎ ዉድቅ እንዲደረግልን እጠየቅን የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በቅጽ 12፤መ/ቁጥር 56794፤ከገጽ 71-74 ላይ በቀብድ ዉል መሠረት የሽያጭ ዉሉ እንዲፈጸም መጠየቅ የፍ/ሕ/ቁጥር 1885 ስር የተደነገገዉን የሚጥስና መሠረታዊ የህግ ስህተት የሚያስከትል ነዉ በማለት ከሰጠዉ የህግ ትርጉም አንጻር ከሳሽ በቀብድ ዉል መሠረት እንዲፈጸምለት መጠየቁ የህግ ድጋፍ የለዉም ተብሎ ዉድቅ እንዲደረግልን እየጠየቅን ከሳሽ በቀብድ ዉሉ መሰረት ግዴታዉን ባለመወጣቱ የተነሳ ተከሳሾች ቤቱን በሰኔ 28 ቀን 2013ዓ.ም ለአቶ እንድሪስ ጀማል እና ንቅ ትሬዲንግ አ.ማህበር በሽያጭ ያስተላለፍን በመሆኑ በቀብድ ዉሉ መሰረት የሚፈጸም የሽያጭ ዉል ወይም የቤት ርክክብ የለም ተብሎ እንዲወሰንልን እንዲሁም የተከበረዉ ፍ/ቤት ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም በተፈጸመዉ ዉል መሠረት ያልፈጸመዉና ዉሉን ያፈረሰዉ ከሳሽ ራሱና በራሱ ምክንያት ነዉ ተብሎ ከሳሽ የከፈለዉን ቀብድ ተከሳሾች ሊመልሱ አይገባም ተብሎ እንዲወሰንልንና በከሳሽ ያለአግባብ ክስ ምክንያት ተከሳሾች ላወጣነዉ ወጪና ኪሳራ ከሳሽን
የመጠየቅ መብታችን ተጠብቆ ዉሳኔ እንዲሰጥልን በማለት ዉሳኔ እንዲሰጥልን በማለት ጠይቀዋል፡፡ የሰውና የሰነድ ማስረጃ ዝርዝር አያይዘው አቅርበዋል፡፡
ፍ/ቤቱ ህዳር 07 ቀን 2014 ዓ.ም በዋለው ችሎት የግራ ቀኙን ክስ የሰማ ሲሆን ግራ ቀኙ ክስ እና የመከላከያ መልሳቸውን በማጠናከር የተከራከሩ በመሆኑ እና ከጽሁፍ ክርክራቸው የተለየ ያላቀረቡ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ በድጋሚ ክርክራቸውን በፍርዱ ላይ ማስፈር ያላስፈለገው በመሆኑ ታልፏል፡፡
ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክስ ከሰማ በኋላ በማስረጃ ሊረጋገጡ የሚገባቸውን ጭብጦች የለየ ሲሆን በዚህም መሰረት ግራ ቀኙ ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም ባደረጉት የቤት ሽያጭ ውል ስምምነት እንደውሉ ያልፈፀሙት ተከሳሽ ናቸው ወይስ ተከሳሾች? በዚህ ግራ ቀኙ ባደረጉት የቤት ሽያጭ ውል ላይ በተመለከተው አግባብ የሽያጭ ገንዘቡን ለተከሳሾች ከፍለዋል ወይስ አልከፈሉም? አከፋፈሉን በተመለከተስ ግራ ቀኙ ውሉን አሻሽለውታል ወይስ አላሻሻሉትም? ከሳሽ የሽያጩን ገንዘብ በአንድ ጊዜ ከሚከፈለው በመጠን ቀንሰው ወይም ጨምረው መክፈላቸውን እንዲሁም የሚከፈልበትን ቀን አዛብተው ከፍለዋል ወይስ አልከፈሉም ከፍለው ከሆነስ ውጤቱ ምንድን ይሆናል በአጠቃላይ ተከሳሾች ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም በተደረገው የቤት ሽያጭ ውል መነሻነት የተከፈላቸውን የቀብድ ገንዘብ አጠፌታውን ሊከፍሉ ይገባል ወይስ አይገባም የቤቱን ስመ ሀብት ለከሳሽ ሊያዛውሩ ይገባል ወይስ አይገባም የሚሉ ዋና ጭብጦችን እና ሌሎች ተያያዥ ፍሬ ነገሮችን ከቀረቡት የሰነድ ማስረጃዎች በተጨማሪ በግራ ቀኙ ምስክሮች ጭምር ማጣራት አስፈላጊ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ምስክሮች ሰምቷል፡፡
በዚህም መሰረት ከሳሽ ሶስት የሰው ምስክሮችን አቅርበው ያሰሙ ሲሆን የግራ ቀኙ የጋራ ምስክር በችሎት ቀርበው ሲመሰክሩ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ወረዳ 02 የሆነውን እና የቤት ቁጥሩን የማላስታውሰው ቤት ለከሳሽ ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም በተደረገ የሽያጭ ውል ሲሸጥ በውሉ ላይ በምስክርነት ነበርኩኝ፤ የሽያጩ ዋጋ ብር 7,650,000.00/ሰባት ሚሊዮን ስድስት መቶ ሀምሳ ሺህ/ ሲሆን አከፋፈሉን በተመለከተም 650,000/ስድስት መቶ ሀምሳ ሺህ/ ለሁለተኛ ተከሳሽ ገቢ በማድረግ ከፍለዋል፡፡ ቀጣዩን ብር 4,000,000.00/አራት ሚሊዮን/ ሰኔ
18 ቀን 2013 ዓ.ም ለመክፈል ቀሪውን ብር 3,000,000/ሶስት ሚሊዮን/ ደግሞ ሐምሌ 2 ቀን 2013 ዓ.ም ከፍለው ሊያጠናቅቁ ግራ ቀኙ ተስማምተዋል ይህን አውቃለሁ በማለት መስክረዋል፡፡
የከሳሽ ሁለተኛ ምስክር በሌላ በኩል ከሳሽ እና የ1ኛ ተከሳሽ ወኪል የሆኑት የ2ኛ ተከሳሽ የ1ኛ ተከሳሽን ቤት በተመለከተ ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም የሽያጭ ውል አድርገዋል፡፡ በውሉ ላይ ምስክር ነበርኩ፤ ከሳሽ ብር 650,000/ስድስት መቶ ሀምሳ ሺህ/ ቃብድ በ2ኛ ተከሳሽ አካውንት ላይ ገቢ አድርገዋል፡፡ የቤቱ አጠቃላይ የሽያጭ ዋጋ ብር 7,650,000/ሰባት ሚሊዮን ስድስት መቶ ሀምሳ ሺህ/ ነው፤ አከፋፈሉን በተመለከተም 4,000,000/አራ ሚሊዮን/ ሰኔ 18 ቀን 2013 ዓ.ም ቀጣዩን ክፍያ ብር 3,000,000/ሶስት ሚሊዮን/ ሐምሌ 02 ቀን 2013 ዓ.ም ለመክፈል ነበር፡፡ ሰኔ 18 ቀን 2013 ዓ.ም ሊከፈል የነበረውን ለሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም ለማድረግ ተነጋግረናል በማለት ከሳሽ ነግረውኛል በስልክም ሲያወሩ ሰምቻለሁ፡፡ ሰኔ 21 ቀን ከሳሽ እና 2ኛ ተከሳሽ ተቀጣጥረው አብረን ሄደን ለ2ኛ ተከሳሽ ከሳሽ ስልክ ሲደውሉ ስልክ ሳያነሱ ቀርተዋል፡፡ ሰኔ 28 ቀን 2013 ዓ.ም 2ኛ ተከሳሽ የአቢሲንያ ባንክ ሂሳባቸውን ለከሳሽ ልከው ከሳሽ ብር 2,000,000/ሁለት ሚሊዮን/ ገቢ አድርገዋል፡፡ ከዚያ በኋላ 2ኛ ተከሳሽ ሊገኙ ባለመቻላቸው ከሳሽ ሐምሌ 02 ቀን 2013 ዓ.ም ማስጠንቀቂያ በፖስታ ቤት ለ2ኛ ተከሳሽ ልከዋል በማለት መስክረዋል፡፡
የከሳሽ 3ኛምስክር በሌላ በኩል ከሳሽ እና 2ኛ ተከሳሽ ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም የቤት ሽያጭ ውል ሲፈፅሙ አይቻለሁ፤ የሽያጭ ገንዘቡ ብር 7,650,000/ሰባት ሚሊዮን ስድስት መቶ ሀምሳ ሺህ/ ነበር፤ አከፋፈሉን በተመለከተ ውሉ በተደረገበት ዕለት ብር 650,000/ስድስት መቶ ሀምሳ ሺህ/ ከሳሽ ከፍሏል፡፡ አከፋፈሉን በተመለከተ በጽሁፍ ተመልክቷል፤ ከሳሽ ብር 2,000,000/ሁለት ሚሊዮን/ በሁለተኛ ተከሳሽ የባንክ ሂሳብ ገቢ አድርገዋል፡፡ ቀሪው ክፍያ ይፈፀም አይፈፀም አላውቅም፡፡ ከሳሽ ቤቱን እንዳልተረከቡ ነግረውኛል፡፡ ከሳሽ ክስ መመስረታቸውን ነው የማውቀው ሌላ አላውቅም በማለት መስክረዋል፡፡
ተከሳሾች በበኩላቸው የከሳሽን አንደኛ ምስክር ጨምሮ ሶስት ምስክሮችን አቅርበው ያሰሙ ሲሆን የጋራ ምስክሩ ቀደም ሲል ቀርበው የሰጡት ምስክርነት ይዘቱ በአጭሩ በፍርዱ የተመለከተ በመሆኑ በድጋሚ ማስፈር አስፈላጊ ሆኖ አልተገኘም፡፡ የተከሳሾች አንደኛ ምስክር በችሎት ቀርበው 2ኛ ተከሳሽ የ1ኛ ተከሳሽ ወኪል በመሆናቸው ንብረትነቱ የ1ኛ ተከሳሽ የሆነውን ቤት ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም በተደረገ የቤት ሽያጭ ውል ለከሳሽ ሸጠዋል፤ ውሉን ሲዋዋሉ በቦታው ነበርኩ ግን ውሉ ላይ አልፈረምኩም፡፡ የሽያጭ ገንዘቡ ብር 7,650,000/ሰባት ሚሊዮን ስድስት መቶ ሀምሳ ሺህ/ ነበር፤ ውሉ በተደረገበት ዕለት ከሳሽ ብር 650,000/ስድስት መቶ ሀምሳ ሺህ/ ቅድመ ክፍያ ለ2ኛ ተከሳሽ ከፍለዋል፡፡ ሰኔ 18 ቀን 2013 ዓ.ም ብር 4,000,000/አራት ሚሊዮን/ ለመክፈል ተስማተዋል፤ ሐምሌ 2 ቀን 2013 ዓ.ም ደግሞ
ቀሪውን 3,000,000/ሶስት ሚሊዮን/ ለመክፈል ተስማምተዋል፡፡ በውሉ መሰረት ከሳሽ ክፍያውን እንዲፈፅሙ 2ኛ ተከሳሽ መጠየቃቸውን አውቃለሁ፡፡ ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም በጽሁፍ ለከሳሽ አሳውቀዋቸዋል ይህን አውቃለሁ በማለት መስክረዋል፡፡
ሁለተኛ የተከሳሾች ምስክርም ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም ግራ ቀኙ የቤት ሽያጭ ውል አድርገዋል፤ የሽያጩ ገንዘብ ብት 7,650,000/ሰባት ሚሊዮን ስድስት መቶ ሀምሳ ሺህ/ ነበር፤ ውሉ በተደረገበት ዕለት ከሳሽ ለ2ኛ ተከሳሽ ብር 650,000.00/ስድስት መቶ ሀምሳ ሺህ/ ቀብድ ከፍለዋል፡፡ ከሳሽ ብር 4,000,000/አራት ሚሊዮን/ ሰኔ 18 ቀን 2013 ዓ.ም ቀሪውን ብር 3,000,000/ሶስት ሚሊዮን/ ሐምሌ 02 ቀን 2013 ዓ.ም ለመክፈል በውሉ ተስማምተው ነበር፡፡ ሲዋዋሉ በቦታው ነበርኩ፡፡ 2ኛ ተከሳሽ ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም ከሳሹ ክፍያ እንዲፈፅምለት ለከሳሽ ደብዳቤ ሰጥቶ ከሳሽ ደብዳቤውን ተቀብሎ ሄዷል፡፡ ከዚህ ውጪ ሌላ ክፍያ ሲከፈል አላየሁም፡፡ በሌላ ቀን ከሳሽ ብር 2,000,000/ሁለት ሚሊዮን/ በባንክ ገቢ አደረገልኝ ብሎ ነግሮኛል፡፡ ከሳሽ ብር 2,000,000/ሁለት ሚሊዮን/እንዴት እንዳስገባ አላውቅም በማለት መስክረዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ምስክሮች ከሰማ በኋላ ቀደም ሲል የተለዩትን ጭብጦች ግራ ቀኙ ካቀረቧቸው የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች እዲሁም አግባብነት ካላቸው የሕግ ድንጋጌዎች አኳያ እንደሚከተለው ተመርምሯል፡፡
እንደተመረመረውም የመጀመሪያውን ጭብጦች ማለትም ግራ ቀኙ ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም ባደረጉት የቤት ሽያጭ ውል ስምምነት እንደውሉ ያልፈፀሙት ከሳሽ ናቸው ወይስ ተከሳሾች? በዚህ ግራ ቀኙ ባደረጉት የቤት ሽያጭ ውል ላይ በተመለከተው አግባብ የሽያጭ ገንዘቡን ከሳሽ ለተከሳሾች ከፍለዋል ወይስ አልከፈሉም? አከፋፈሉን በተመለከተስ ግራ ቀኙ ውሉን አሻሽለውታል ወይስ አላሻሻሉትም? ከሳሽ የሽያጩን ገንዘብ በአንድ ጊዜ ከሚከፈለው በመጠን ቀንሰው ወይም ጨምረው መክፈላቸውን እንዲሁም የሚከፈልበትን ቀን አዛብተው ከፍለዋል ወይስ አልከፈሉም ከፍለው ከሆነስ ውጤቱ ምንድን ይሆናል የሚለውን በተመለከተ ከሳሽ ያቀረቡት ክርክር 1ኛ ተከሳሽ በስማቸው ተመዝግቦ የሚገኝ እና የካርታ ቁጥሩ 02/263/0017225/00 የሆነ በቀድሞው ወረዳ 23 ቀበሌ 14 በአሁኑ ወረዳ 2 ክልል ይዞታ ያላቸው ሲሆን 1ኛ ተከሳሽ ይህንኑ ይዞታ በማስመልከት በውክልና ቁጥር 14/0002061/1/2012 በቀን 14/12/2012 ዓ.ም ለ2ኛ ተከሳሽ በን/ስ/ላፍቶ ክ/ከተማ ወረዳ 02 ክልል ውስጥ የሚገኘውን የግል ይዞታቸውን ለመሸጥ፣ ለመለወጥ እንዲሁም የሽያጩን ገንዘብ
ለመቀበል የሚያስችል ውክልና የሰጡ ሲሆን 2ኛ ተከሳሽ ይህንኑ የመኖሪያ ቤት ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም በተደረገ የሽያጭ ውል ለከሳሽ በብር 7,650,000.00/ሰባት ሚሊዮን ስድስት መቶ ሀምሳ ሺህ/ ሸጠው በእለቱም በውሉ ደረሰኝነት ከሽያጭ ገንዘቡ ላይ ብር 650,000.00/ስድስት መቶ ሀምሳ ሺህ/ ቃብድ ተቀብለው እና በከሳሽና በተከሳሾች መካከል በተደረገው የስልክ ልውውጥ ከቀሪው የሽያጭ ገንዘብ ውስጥ ብር 2,000,000.00/ሁለት ሚሊዮን/ በቀብድነት እንዲሰጣቸው ወይም እንዲላክላቸው ጠይቀው በተደረሰው ስምምነት በ2ኛ ተከሳሽ ስም በአቢሲኒያ ባንክ መካኒሳ ቅርንጫፍ በሂሳብ ቁጥር 68126819 ሰኔ 29 ቀን 2013 ዓ.ም ገቢ አድርጌላቸው ቤት ሽያጭ ውል ስምምነት መሰረት ተከሳሾች ቀሪውን የሽያጭ ገንዘብ ብር 5,000,000.00/አምስት ሚሊዮን/ተቀብለው ቤቱን እና የቤቱን ሰነዶች እንዲያስረክቡን እንዲሁም የቤቱን ሽያጭ ቀሪ ገንዘብ ከመቀበላቸው በፊት በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ቀርበው የውል ግዴታቸውን እንዲወጡ በተደጋጋሚ ብጠይቃቸውም ሊፈፅሙ ፍቃደኛ ሆነው ባለመገኘታቸው ከሳሽ በጠበቃዬ በኩል ሰኔ 22 ቀን 2013 ዓ.ም ለ1ኛ ተከሳሽ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ሰጥቻለሁ፡፡ በመሆኑም ተከሳሾች ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም በተደረገው የሽያጭ ውል መነሻነት በውሉ ተመለከተውን ቤትና ይዞታ ቀሪ የሸያጭ ገንዘባቸውን ተቀብለው ቤቱን እና የቤቱን ሰነዶች ለከሳሽ እንዲያስረክቡና የቤቱን ስመ ሀብት እንዲያዛውሩ እንዲወስንልን ተከሳሾች በየሽያጭ ውል መሰረት ለመፈፀም ፍቃደኛ ካልሆነኑ በውሉ ደረሰኝነት የወሰዱትን ብር 650,000/ስድስት መቶ ሀምሳ ሺህ/ እንዲሁም ሰኔ 29 ቀን 2013 ዓ.ም ከከሳሽ የሂሳብ ቁጥር 68693993 ወደ 2ኛ ተከሳሽ የባንክ ሂሳብ ቁጥር 68126819 ገቢ የተደረገውን ብር 2,000,000.00/ሁለት ሚሊዮን/ በአጠቃላይ ብር 2,650,000.00/ሁለት ሚሊዮን ስድስት መቶ ሀምሳ ሺህ/ ቃብድ የተቀበሉ በመሆኑ የዚህን ገንዘብ አጠፌታ ተከሳሾች ለከሳሽ እንዲከፍሉ ይወሰንልን የሚል ነው፡፡
ተከሳሾች በበኩላቸው ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም የቤት ሽያጭ ውል መደረጉ የሚካድ አይደለም፤ በውሉ መሰረት በዕለቱ ከሳሽ ብር 650,000/ስድስት መቶ ሀምሳ ሺህ/ ቀብድ ለመክፈል ተስማምተው የከፈሉ ሲሆን ቀሪውን የቤት ሽያጭ ገንዘብ በውሉ በተመለከተው አግባብ ሰኔ 18 ቀን ብር 4,000,000/አራት ሚሊዮን/፣ ሐምሌ 2 ቀን 2013 ዓ.ም ደግሞ ብር 3,000,000/ሶስት ሚሊዮን/ ለመክፈል የተስማማን ቢሆንም ከሳሽ በውሉ በተመለከተው ሁኔታ ገንዘቡን በመክፈል ሀላፊነታቸውን አልተወጡም፡፡ በውሉ በተመለከተው አግባብ መክፈል ሲጠበቅበት ይህን ግዴታዉን ሳይወጣ በመቅረቱ ዉሉን ያፈረሰዉ ከሳሽ ራሱ እንጂ ተከሳሾች አይደለንም፡፡ ከሳሽ በዉል ላይ በተቀመጠዉ ጊዜ ክፍያ ባለመክፈሉ የተነሳ ተከሳሾች ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም
ማስጠንቀቂያ የሰጠነዉ ቢሆንም በማስጠንቀቂያዉ መሠረትም ግዴታዉን ሳይወጣ ቀርቷል፡፡ ከሳሽ በክስ አቤቱታዉ ላይ ብር 2,000,000(ሁለት ሚሊየን ብር) በቀብድነት እንዲላክላቸዉ በተደረገዉ ስምምነት በ2ኛ ተከሳሽ በአቢሲኒያ ባንክ መካኒሳ ቅርንጫፍ በሂሳብ ቁጥራቸዉ ሰኔ
29 ቀን 2013ዓ.ም ገቢ አድርጊያለሁ ቢልም በዉላችን ላይ ስለ ሁለት ሚሊየን ብር ክፍያ ጭራሹኑ የሌለ ከመሆኑም በተጨማሪ ቀደም ሲል የፈጸምነዉ በሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም የሽያጭ ውል በጽሁፍ እንደመደረጉ መጠን ይህን ዉል በሌላ ጽሁፍ ዉል ስለመተካቱ ያቀረበዉ ምንም ማስረጃ በሌለበት ከሳሽ በራሱ ጊዜ ሊያዉም ተከሳሾች ማስጠንቀቂያ ከሰጠንበት እንዲሁም በዉሉ ላይ ከተቀመጠዉ ቀናት እና የገንዘብ መጠን ዉጪ ተከሳሸ ገቢ ያደረገዉ ብር 2,000,000.00(ሁለት ሚሊየን) በምንም መልኩ በዉሉ መሠረት ከሳሽ ግዴታዉን ተወጥቷል ሊያሰኝ አይችልም፤ ይህን ብር ከሳሽ ካስገባ በኃላ በቅንነት ከዉላችን ዉጪ ያስገባዉን 2,000,000ብር(ሁለት ሚሊየን ብር) መዉሰድ ትችላለህ፤ይመለስልህ ስንለዉም ከሳሽ ፈቃደኛም አልነበረም፡፡ አሁንም ቢሆን ይህን ከሳሽ ከዉል ዉጪ ገቢ ያደረገዉን 2,000,000ብር(ሁለት ሚሊየን ብር) መዉሰድ ይችላል፡፡ በመሆኑም በሰኔ 17 ቀን 2013ዓ.ም የተጻፈዉ ዉል ያፈረሰዉና ያልፈጸመዉ ከሳሽ ራሱ በመሆኑ በፍ/ሕ/ቁጥር 1885(2) መሰረት በዉሉ መሠረት ያልተፈጸመዉ ወይም ዉሉን ያፈረሰ ከሳሽ በመሆኑ በዉል ላይ የተጠቀሰዉን ቀብድ ከሳሽ መጠየቅ ስለማይችል የተከበረዉ ፍ/ቤት የከሳሽን ክስ ዉድቅ በማድረግ ዉሳኔ እንዲሰጥልን በከሳሽና ተከሳሸ መካከል ግልጽ ዉል ባለበት እና የቀብድ ገንዘቡም መጠን በግልጽ ተቀምጦ ባለበት ከሳሽ ሆነ ብሎ የቀበድ ገንዘቡ ብር 2,650,000(ሁለት ሚሊየን ስድስት መቶ ሀምሳ ሺህ) በማለት ያቀረበዉ ክስ አግባብነት የሌለዉና የቀብድ ዉል ህግጋትን የጣሰ ነዉ፡፡ ዉል ለመለወጥም ሆነ ለማሻሻል ወይም ተጨማሪ ዉል ለማድረግ በፍ/ሕ/ቁጥር 1722 መሠረት በጽሁፍ መደረግ እንደሚገባዉ ከተደነገገዉ የህግ ደንጋጌ አንጻርም የከሳሽ የክስ ፍሬ ነገር የሕግ ድጋፍ የለዉም፡፡ በመሆኑም የተከበረዉ ፍ/ቤት ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም በተፈጸመዉ ዉል መሠረት የቀብድ ገንዘብ መጠኑ ብር 650,000(ስድስት መቶ ሀምሳ ሺህ) እንጂ ብር 2,650,000(ሁለት ሚሊየን ስድስት መቶ ሀምሳ ሺህ) አይደለም እንዲባልልን፣ ከሳሽ በክሰ አቤቱታዉ ላይ በሰኔ 17 ቀን 2013ዓ.ም በተጸፈመ የቤት ሽያጭ ዉል መሠረት ተከሳሾች ቀሪ ገንዘባቸዉን 5,000,000ብር(አምስት ሚሊየን ብር) ተቀብለዉ ቤቱንና የቤቱን ሰነድ በህግ ሀይል ተገደዉ እንዲያስረክቡኝ እና ወደ ሚመለከተዉ መንግስታዊ አካል ቀረበዉ ስመ ሀብቱን እንዲያዛዉሩ በማለት ያቀረበዉ ክስ ከላይ በዝርዝር እንዳቀረብነዉ በዉሉ መሠረት በከሳሽ
በኩል የሚጠበቀውን ግዴታ ሳይወጣ ተከሳሾች በውሉ የተመለከተ ግዴታቸውን እንዲወጡ ሊጠይቅ አይችልም በሚል ክርክር ያቀረቡ ስለመሆኑ ከመዝገቡ መረዳት ይቻላል፡፡
ከሳሽ የክስ አቤቱታቸውን ለማስዳት የሰውና የሰነድ ማስጃዎችን አያይዘው ያቀረቡ ሲሆን በሰነድ ማስረጃዎች ረገድ ግራ ቀኙ ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም ያደረጉትን የመኖሪያ ቤት ሽያጭ ውል፣ ለክርክሩ መነሻ የሆነውን የካርታ ቁጥሩ 03/263/0017225/00 የሆነና በ1ኛ ተከሳሽ ስም የተሰጠ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታን፣ 1ኛ ተከሳሽ ለ2ኛ ተከሳሽ የሰጡትን ሕጋዊ ውክልና፣ ከሳሽ ለ2ኛ ተከሳሽ ብር 2,000,000/ሁለት ሚሊዮን/ ገቢ ያደረጉበትን የባንክ ደረሰኝ እንዲሁም ከሳሽ በጠበቃቸው በኩል ለተከሳሾች የሰጡት ሕጋዊ ማስጠንቀቂያን በሰነድ ማስረጃነት አያይዘው አቅርበው በፍርድ ቤቱ ተመርምሯል፡፡
ተከሳሾች በበኩላቸው የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን አያይዘው ያቀረቡ ሲሆን በሰነድ ማስረጃዎች ረገድ ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም 1ኛ ተከሳሽ በወኪላቸው አማካኝነት ለከሳሽ የሰጡትን ሕጋዊ ማስጠንቀቂያ፣ ተከሳሾች አከራካሪውን ቤት አስመልክቶ ሰኔ 28 ቀን 2013 ዓ.ም ከአቶ እንድሪስ ጀማል እና ንቅ ትሬዲንግ አ.ማ የሽያጭ ውል ያደረጉ ስለመሆኑ የሚያመለክት ውል በሰነድ ማስረጃነት አያይዘው አቅርበዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ በግራ ቀኙ የቀረቡትን የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች መርምሮ የመዘነ ሲሆን ግራ ቀኙ ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም ባደረጉት የቤት ሽያጭ ውል 1ኛ ተከሳሽ በስማቸው ተመዝግቦ የሚገኘውን የካርታ ቁጥሩ 02/263/0017225/00 የሆነ በቀድሞው ወረዳ 23 ቀበሌ 14 በአሁኑ ወረዳ 2 ክልል ውስጥ የሚገኘውን 460 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ የመኖሪያ ቤት በብር 7,650,000.00/ሰባት ሚሊዮን ስድስት ሀምሳ ሺህ/ ለከሳሽ ለመሸጥ ተስማምተው ከሳሽ ውሉ በተደረገበት ዕለት ብር 650,000/ስድስት መቶ ሀምሳ ሺህ/ ከፍለው ሁለተኛውን ክፍያ ብር 4,000,000/አራት ሚሊዮን/ከሳሽ ሰኔ 18 ቀን 2013 ዓ.ም ለተከሳሾች ሊከፍሉ ቀሪውን ገንዘብ ብር 3,000,000/ሶስት ሚሊዮን/ ደግሞ ሐምሌ 02 ቀን 2013 ዓ.ም ለመክፈል ስምምነት ያደረጉ ስለመሆኑ የቀረበው ውል ያስረዳል፡፡ ከሳሽ ሰኔ 29 ቀን 2013 ዓ.ም በአቢሲኒያ ባንክ ከሚገኘው የሂሳብ ቁጥራቸው 68693993 ለ2ኛ ተከሳሽ በሂሳብ ቁትር 68126819 ብር 2,000,000/ሁለት ሚሊዮን ገቢ ያደረጉ ስለመሆኑ እንዲሁም ከሳሽ ሰኔ 30 ቀን 2013 ዓ.ም በተፃፈ ሕጋዊ ማስጠንቀቂያ ከሳሽ ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም በተደረገው የቤት ሽያጭ ውል መነሻነት ብር 650,000/ስድስት መቶ ሀምሳ ሺህ/ መክፈላቸውን እንዲሁም በውሉ መሰረት ብር 2,000,000/ሀለት ሚሊዮን/ በባንክ ሂሳብ ለሻጭ ገቢ የተደረገ መሆኑን እና ከሳሽ ቀሪውን
የቤት ሽያጭ ገንዘብ ብር 5,000,000/አምስት ሚሊዮን/ በቼክ ለተከሳሾች ለመክፈል ያዘጋጁ በመሆኑ ተከሳሾች በውል ግዴታቸው መሰረት በውልና ማስረጃ ቀርበው የቤቱን ስመሀብት እንዲያዛውሩና ቀሪ ገንዘቡን እንዲቀበሉ ይህን ለማድረግ ፍቃደኛ ካልሆኑ ደግሞ በቀብድነት የተቀበሉትን ብር 2,650,000/ሀለት ሚሊዮን ስድስት መቶ ሀምሳ ሺህ/ አጠፌታ የሆነውን ብር 5,300,000/አምስት ሚሊዮን ሶስት መቶ ሺህ/ለከሳሽ እንዲከፈፍሉ በሚል ማስጠንቀቂያ የፃፉ ስለመሆኑ መረዳት ይቻላል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከሳሽ ምን አይነት ሰነድ ለ2ኛ ተከሳሽ መላካቸው ባይረጋገጥም 2ኛ ተከሳሽ ሐምሌ 10 ቀን 2013 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ከከሳሽ የተላከ ሰነድ የተቀበሉ ስለመሆኑ የቀረቡት ሰነዶች የሚያስረዱ ሆነው ተገኝተዋል፡፡
በሌላ በኩል 2ኛ ተከሳሽ ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም በተደረገው የቤት ሽያጭ ውል መሰረት ክፍያ ያልተፈፀመ በመሆኑ በውሉ የተቀመጠውን የገደብ መቀጮ ብር 1,000,000/አንድ ሚሊዮን/ከሳሽ ለ2ኛ ተከሳሽ እንዲከፍሉ የማይከፍሉ ከሆነ ግን ውሉን ከሳሽ በራሳቸው ፍላጎት ያፈረሱ ሆኖ እንደሚቆጠር በማሳሰብ ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም ሕጋዊ ማስጠንቀቂያ ለከሳሽ የፃፉ ስለመሆኑ እና 1ኛ ተከሳሽ ሰኔ 28 ቀን 2013 ዓ.ም በተደረገ ቤት ሽያጭ ውል አከራካሪውን ቤት በብር 6,200,000/ስድስት ሚሊዮን ሁለት መቶ ሺህ/ ለመሸጥ ተስማምተው የሽያጭ ውል የተደረገ ስለመሆኑ የቀረቡት የሰነድ ማስረጃዎች ያስረዳሉ፡፡
በግራ ቀኙ የቀረቡት የሰው ምስክሮችም በበኩላቸው ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም ግራ ቀኙ የቤት ሽያጭ ስምምነት ያደረጉ መሆኑት የቤቱ ሽያጭ ገንዘብ ብር 7,650,000/ሰባት ሚሊዮን ስድስት መቶ ሀምሳ ሺህ/ መሆኑን የገንዘቡ አከፋፈልም ውሉ በተደረገበት ዕለት ብር 650,000/ስድስት መቶ ሀምሳ ሺህ/ በቀብድ ከሳሽ ለ2ኛ ተከሳሽ የከፈሉ ስለመሆኑ እና ሁለተኛው ክፍያ በማግስቱ ሰኔ 18 ቀን 2013 ዓ.ም ብር 4,000,000/አራት ሚሊዮን/ ቀጣዩን የመጨረሻ ክፍያ የሆነውን ብር 3,000,000/ሶስት ሚሊዮን/ ደግሞ ሐምሌ 2 ቀን 2013 ዓ.ም ለመክፈል ግራ ቀኙ የጽሁፍ ስምምነት ያደረጉ መሆኑን እንደሚያውቁ እና ከሳሽ ሰኔ 18 ቀን 2013 ዓ.ም ክፍያውን ባለመፈፀማቸው 2ኛ ተከሳሽ ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ለከሳሽ የሰጡ መሆኑን እንደሚያውቁ መስክረዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከሳሽ ሰኔ 29 ቀን 2013 ዓ.ም ብር 2,000,000/ሁለት ሚሊዮን/በሁለተኛ ተከሳሽ የአቢሲንያ ባንክ ሂሳብ ገቢ ማድረጋቸውን እንደሚያውቁ መስክረዋል፡፡
በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1675 መሰረት ውል ተዋዋይ ወገኖች ንብረታቸውን የሚመለከቱ ግዴታዎችን ለማቋቋም ወይም ለመለወጥ ወይም ለማስቀረት ባላቸው ተወዳዳሪ ግንኙነት የሚያደርጉት ስምምነት ነው፡፡ ተዋዋይ ወገኖች ባቋቋሙት የውል ስምምነት ውስጥ የሚገኝን ግዴታ በፈለጉ ጊዜ የውሉን ቃል በማበር የሚፈፅመው ወይም የሚተወው ሳይሆን በተዋዋይ ወገኖች በሕጉ አግባብ የተቋቋሙ ውሎች ባቋቋሟቸው ሰዎች ላይ ሕግ መሆናቸውን የፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1731(1) በግልፅ ይደነግጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ተዋዋይ ወገኖች አስቀድሞ የነበራቸውን የውል ግንኙነት ለማሻሻል የፈለጉ እንደሆነ በምን አይነት ሁኔታ ሊያሻሽሉና ሊለውጡ እንደሚችሉ የፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1884 እና 1722 ድንጋጌዎች ያስገነዝባሉ፡፡ በዚህ መሰረት የፍ/ብ/ሕ/ቁ 1722 ተዋዋይ ወገኖች ቀደም ብለው ያደረጉትን ዋናውን ውል የመለወጥ ፍላጎት ካላቸው የሚያሻሽሉት ውል ቀደም ሲል በተደረገው የውል ስምምነት አቀራረብ /ፎርም/ መሆን እንዳለበት በግልጽ ይደነግጋል፡፡
አሁን በተያዘው ጉዳይ ከሳሽ ከ1ኛ ተከሳሽ ጋር ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም የቤት ሽጭ ውል ስምምነት አድርገው የሽያጩን ገንዘብ አከፋፈልንም በተመለከተ በውላቸው በግልጽ አስፍረው ግራ ቀኙ ውል አድርገዋል፡፡ ከሳሽ ለ1ኛ ተከሳሽ በውሉ መሰረት ቀብድ ብር 650,000/ስድስት መቶ ሀምሳ ሺህ/ ውል በተደረገበት ዕለት ከፍዬ ከ2ኛ ተከሳሽ ጋር በስልክ ልውውጥ ብር 2,000,000/ሁለት ሚሊዮን/ በባንክ ሂሳባቸው ገቢ እንዳደርግ ተስማምተን ብር
2,000,000/ሁለት ሚሊዮን ብር/ በባንክ ገቢ አድርጌ ተከሳሾች ቀሪ ገንዘባቸውን እንዲወስዱና የቤቱን ስመ ሀብት ለከሳሽ እንዲያዛውሩ እንዲወሰንልኝ ወይም በቀብድ የወሰዱትን ብር 2,650,000/ሁለት ሚሊዮን ስድስት መቶ ሀምሳ ሺህ/አጠፌታውን እንዲከፍሉ ይወሰንልኝ በማለት ክርክር ቢያቀርብም ከሳሽ በውል ስምምነቱ የተመለከተውን አከፋፈል በተመለከተ በግራ ቀኙ መካከል ሕጉ በግልጽ ባስቀመጠው ፎርም የተሻሻለ ስለመሆኑ በአግባቡ በማስረጃ አስደግፈው ያላቀረቡ በመሆኑ ይልቅም በውል ስምምነቱ መሰረት ገንዘቡን ለተከሳሾች ከመክፈል ይልቅ ሰኔ 29 ቀን 2013 ዓ.ም ለ1ኛ ተከሳሽ በባንክ ሂሳባቸው ብር 2,000,000/ሁለት ሚሊዮን/ ገቢ ያደረኩ በመሆኑ ተከሳሾች ተገደው የቤቱን ሰነዶች እንዲስረክቡኝ እና ቀሪ ገንዘባቸውን ተቀብለው የቤቱን ስመሀብት ለከሳሽ እንዲያዛውሩ በማለት ክርክር ማቅረባቸው በውል የገቡትን ግዴታ ያላገናዘበ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በግራ ቀኙ የቀረቡት የሰነድ ማስረጃዎች ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም በተደረገው የቤት ሽያጭ ውል ስምምነት መሰረት እንደውሉ ያልፈፀሙት ከሳሽ ራሳቸው መሆናቸውን እና በውሉ ግራ
ቀኙ ቃብድ እንዲሆን ተስማምተው ክፍያ የተፈፀመበት የገንዘብ መጠንም ብር 650,000/ስድስት መቶ ሀምሳ ሺህ/ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡
ሁለተኛውን ጭብጥ ማለትም ተከሳሾች ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም በተደረገው የቤት ሽያጭ ውል መነሻነት የተከፈላቸውን የቀብድ ገንዘብ አጠፌታውን ሊከፍሉ ይገባል ወይስ አይገባም እና የቤቱን ስመ ሀብት ለከሳሽ ሊያዛውሩ ይገባል ወይስ አይገባም የሚለውን በተመለከተ ከላይ በዝርዝር እንደተመለከተው ግራ ቀኙ ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም ባደረጉት የሽያጭ ውል መሰረት የሽያጭ ገንዘቡን በውሉ በተመለከተው አግባብ ያልከፈሉ ስለመሆኑ በአግባቡ በግራ ቀኙ ማስረጃዎች የተረጋገጠ ሲሆን ከሳሽ ለተከሳሾች ብር 2,650,000/ሁለት ሚሊዮን ስድስት መቶ ሀምሳ ሺህ/ መክፈላቸውን እና ቀሪውን ገንዘብ ለተከሳሾች ከፍለው የቤቱን ሰነዶች እንዲያስረክቧቸው እና የቤቱን ስመሀብት እንዲያዛውሩ እንዲወሰን ተከሳሾች በውሉ መሰረት ለመፈፀም ፍቃደኛ ካልሆኑ ግን በቀብድነት የተቀበሉትን ብር 2,650,000/ሁለት ሚሊዮን ስድስት መቶ ሀምሳ ሺህ/ አጠፌታ እንዲከፍሉ በማለት ክርክር ያቀረቡ ቢሆንም ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም በተደረገው የቤት ሽያጭ ውል መሰረት ያልፈፀሙት ራሳቸው ከሳሽ ስለመሆናቸው የተረጋገጠ በመሆኑ እና በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰበር መዝገብ ቁጥር 56794 ላይ ተዋዋይ ወገኖች የሽጭ ውል ሲያደርጉ በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1885 ስር በተመለከተው አግባብ ውሉን ሊያፈርሱ የሚችሉበትን አግባብ ቀሪ ያደረጉ ስለመሆኑ የቀረበ ማስረጃ የሌለ በመሆኑ ከሳሽ በውሉ መሰረት ሳይፈፅሙ ተከሳሾች በውሉ መሰረት እንዲፈፅሙ በማለት መጠየቃቸው ተገቢነት የሌለው በመሆኑ ፍርድ ቤቱ የከሳሽን ክርክር አልተቀበለውም፡፡
ከሳሽ በግራ ቀኙ መካከል በተደረገው የውል ስምምነት መሰረት ስላልፈፀሙ ተከሳሾች ውሉን የማፍረስ መብት ያላቸው በመሆኑ በቀብድ የተቀበሉትን ብር 650,000/ስድስት መቶ ሀምሳ ሺህ/ አጠፌታውን ለከሳሽ የሚከፍሉበት ምክንያት ባለመኖሩ ከሳሽ በዚህ ረገድ ያቀረቡትን ዳኝነት ፍርድ ቤቱ ያልተቀበለው ሲሆን ተከሳሾች አከራካሪውን ቤት ሰኔ 28 ቀን 2013 ዓ.ም በተደረገ የቤት ሽያጭ ውል ለሌላ ሶስተኛ ወገን በሽያጭ ያስተላለፉት በመሆኑ እና ከሳሽ ራሳቸው በውል የገቡትን ግዴታ በአግባቡ ሳይወጡ ሌላኛው ወገን የውል ግዴታውን እንዲወጣ ሊጠይቁ ስለማይችሉ ተከሳሾች ለከሳሽ ቤቱን ተገደው ሊያስረክቡ የሚገዱዱበት ምክንያት የለም ተብሏል፡፡
1. በአጠቃላይ ከላይ በዝርዝር በተመለከተው ምክንያት ከሳሽ ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም በተደረገው የቤት ሽያጭ ውል መሰረት የውል ግዴታቸውን ያልተወጡ መሆኑን እና
ተከሳሾች በፍ/ብ/ህ/ቁ. 1885/1 የተመለከተው ድንጋጌ ለግራ ቀኙ የውል ድንጋጌ ተፈፃሚነት እንዳይኖረው ስምምነት ያደረጉ ስለመሆኑ በማስረጃ አስደግፈው ያላቀረቡ በመሆኑ እና ከሳሽ በውሉ በገቡት ግዴታ መሰረት ክፍያውን በወቅቱ ያልከፈሉ ስለመሆኑ በግራ ቀኙ ማስረጃዎች በሚገባ የተረጋገጠ በመሆኑ ተከሳሾች በውሉ መሰረት የተቀበሉትን ቃብድ የሚመልሱበትም ሆነ የቤቱን ስመ ሀብት ለከሳሽ ለማዛወር የሚገደዱበት ሕጋዊ ምክንያት የሌለና ከሳሽ ሰኔ 29 ቀን 2013 ዓ.ም አቢሲንያ ባንክ ካላቸው ሂሳብ ላይ ተቀንሶ ለ2ኛ ተከሳሽ የተከፈለው ብር 2,000,000/ሁለት ሚሊዮን/ ተከሳሾች ለከሳሽ ሊመልሱላቸው ይገባል በማለት ፍርድ ቤቱ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 273 መሰረት ፍርድ ሰጥቷል፡፡
ው ሳ ኔ
2. ግራ ቀኙ ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም ባደረጉት የቤት ሽያጭ ውል እንደውሉ ያልፈፀሙት ከሳሽ በመሆናቸው ተከሳሾች በቃብድ የተቀበሉትን ብር 650,000.00/ስድስት መቶ ሀምሳ ሺህ/ ለከሳሽ የሚመልሱበትም ሆነ የአከራካሪውን ቤት ስመ ሀብት ወደ ከሳሽ እንዲዛወር የማድረግ ግዴታ የለባቸውም ተብሎ ተወስኗል፡፡
3. ከሳሽ ሰኔ 29 ቀን 2013 ዓ.ም አቢሲንያ ባንክ ካላቸው ሂሳብ ላይ ተቀንሶ ለ2ኛ ተከሳሽ የተከፈለው ብር 2,000,000/ሁለት ሚሊዮን/ ለከሳሽ ተከሳሾች ሊመልሱላቸው ይገባል ተብሎ ተወስኗል፡፡
4. ወጪ ኪሳራን በተመለከተ ተከሳሾች የወጪ ኪሳራ ዝርዝር አቤቱታ የማቅረብ መብታቸው ተጠብቋል፡፡
ት ዕ ዛ ዝ
1. በፍርዱ እና ውሳኔው ቅር የተሰኘ ወገን ይግባኝ የማለት መብቱ የተጠበቀ ነው፡፡
2. መዝገቡ በውሳኔ እልባት ያገኘ በመሆኑ ተዘግቶ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡
የማይነበብ የዳኛ ፊርማ አለበት፡፡