አዋጁን ለማሻሻል ያስፈለገባቸዉ ዋና ዋና ምክንያቶችና የማሻሻሉ ሂደት. 2.1 አዋጁን ለማሻሻል ያስፈለገበት ዋነኛዉ ምክንያት አገራችን በጀመረችዉ አጠቃላይ አገራዊ የሪፎርም አጀንዳ ማዕቀፍ ዉስጥ በክፍያ ሥርዓት ዘርፍ አስፈላጊዉን የፖሊሲ ማሻሻያ በማድረግ በተለይም የመንግሥትን የፖሊሲ አቅጣጫ መሠረት በማድረግና የክፍያ አገልግሎት ሰጪዎችን ተሳትፎ በማስፋት የክፍያ ሥርዓቱን ዉጤታማነት፣ አስተማማኝነት፣ አካታችነትና ተወዳዳሪነት ለማጎልበት ታስቦ ነዉ፡፡ 2.2 ሥራ ላይ ከዋለ ከ10 ዓመታት በላይ ሳይሻሻል የቆየዉ አዋጅ ያልሸፈናቸዉን ሆኖም ገበያዉ አበክሮ የሚፈልጋቸዉንና በዘርፉ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተደረጉትን ለዉጦች፣ዕድገቶችና መሻሻሎች ታሳቢ ባደረገ መልኩ ከተለያዩ አገሮች የተገኙትን መልካም ተሞክሮዎች፣ ከዓለም አቀፍ መርሆችና ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማቀናጀት በአዋጁ ዉስጥ ለማካተትና የቁጥጥር ማዕቀፉንም ለማጠናከር ታስቦ ነዉ፡፡ 2.3 የአዋጁ ረቂቅ ማሻሻያ በብሔራዊ ባንክ ቦርድ የታየ ነዉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከመንግሥትና ከአገር ውስጥ የግል የዘርፉ ተዋናዮች ጋር የምክክር መድረክ ተካሂዷል፡፡ ከተደረገዉ ምክክር ጠቃሚ ግብዓት ተገኝቷል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በዘርፉ ሰፊ ልምድና ተሞክሮ ካላቸዉ የዓለም ባንክ ባለሙያዎችም ጠቃሚ ግብዓት ተወስዷል፡፡ 3.