ልዩ ፍላጎት ላላቸው ህፃናት የተመደበ ተጨማሪ የት/ቤቶች ድጎማ በጀት. ልዩ ፍላጉት ያላቸውን ህፃናት በትምህርት ድጋፍ ለማድረግና አመቺ የትምህርት አካባቢ እንዲኖራቸው ለመርዳት እንዲሁም የት/ቤቶች መገልገያዎች ለእነዚህ ህፃናት አመቺ እንዲሆኑ ለማድረግ ከትምህርት አመራር መረጃ ስርዓት በተገኘ መረጃ መነሻነት በ2008 በጀት ዓመት ክልሎች ከሚደርሳችው ጠቅላላ በጀት አንድ በመቶ ለልዩ ፍላጎት ተማሪዎች እንዲውል ተመድቦ የነበረ ሲሆን ክልሎች በክልላቸው ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ተግባራዊ ሲያደርጉ ቆይተዋል። በዚህም መሰረት በት/ቤት መሻሻል ፕሮግራም አተገባበርና በት/ቤት ድጎማ በጀት አጠቃቀም ላይ በተከናወነ ጥናት እንዲሁም ከልማት አጋሮች ጋር በመተባበር በተከናወነ የጋራ ግምገማና ክልላዊ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት በአንዳንድ ክልሎች በመመሪያው መሰረት ልዩ ፍላጎት ያላቸው ት/ቤቶችንና የተማሪዎችን ቁጥር በመለየት ባለድርሻዎችን በማሳተፍ ለተማሪዎቹ አስፈላጊ የትምህርት መሳሪዎች በመግዛት ተማሪዎቹ እንዲጠቀሙባቸው አድርገዋል። በሌላ በኩል አንዳንድ ክልሎችና ወረዳዎች ከመመሪያው ውጪ ለተማሪዎች ቀጥታ የኪስ ገንዘብ የሰጡበት ሁኔታ ታይቷል። በመሆኑም ውጤታማ በሆነ መልኩ ያከናወኑ ክልሎችና ወረዳዎችን ልምድ በመውሰድ ልዩ ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎች ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ በ2009 በጀት ዓመት ለሁሉም ክልሎች ተጨማሪ 2% የት/ቤቶች ድጎማ በጀት እንዲመደብ ተደርጓል፡፡