በአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፕሮግራም /GEQIP/ ለልዩ ፍላጎት ትምህርት ተማሪዎች የተፈቀደውን 2 በመቶ የትምህርት ቤቶች ድጎማ አጠቃቀምን አስመልክቶ የተዘጋጀ የማብራሪያ ሰነድ
በአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፕሮግራም /GEQIP/ ለልዩ ፍላጎት ትምህርት ተማሪዎች የተፈቀደውን 2 በመቶ የትምህርት ቤቶች ድጎማ አጠቃቀምን አስመልክቶ የተዘጋጀ የማብራሪያ ሰነድ
መግቢያ
ትምህርት ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ መሆን ያለበት መሠረታዊ ሰብዓዊ መብት መሆኑ አለም አቀፍ እውቅና የተሰጠው ጉዳይ ነው፡፡ ትምህርት በማንኛውም ማህበረሰብ ውስጥ ድህነትን ለማጥፋትና ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገትን ለማምጣት ምትክ የሌለው ሚና የሚጫወት መሣሪያ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት ልዩ ፍላጎት ላላቸው ዜጎች ትኩረት በመስጠት በህገመንግሥቱ የዜግነት መብቶቻቸው እንዲከበሩ በተመሳሳይም የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲው ውስጥ በፍትሀዊነት የትምህርት ዕድል የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲካተት አድርጓል፡፡ በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገ መንግሥት ዜጎች መንግሥት ባዘጋጃቸው የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ሁሉ እኩል የመጠቀም መብት እንዳላቸውና በተለይም ለአካል ጉዳተኞች አቅም በፈቀደ መጠን ድጋፍ እንደሚያደርግ ደንግጓል (አንቀፅ 41 ንዑስ አንቀፅ 5)፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የአስፈፃሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 916/2008 ውስጥ ከትምህርት ሚኒስቴር ስልጣንና ተግባራት አንዱ “የአካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያን፣ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችና በደማቸው ውስጥ የኤች አይ ቪ ኤድስ ያለባቸው ሰዎች በኃላፊነቱ ክልል የእኩል እድል ተጠቃሚና ሙሉ ተሳታፊ የሚሆኑበትን ሁኔታ ያመቻቻል” በሚል ተግባሩን ይገልጻል፡፡ በዚህም መሰረት የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲው አካል ጉዳተኛና ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ህፃናትና ወጣቶች እንደችሎታቸውና ፍላጎታቸው መማር እንደሚገባቸው ይገልጻል። ይህንን እውን ለማድረግ ጥረት ቢደረግም አሁንም ቢሆን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አካል ጉዳተኛ ህፃናት፣ ወጣቶችና ጎልማሶች የትምህርት እድል ያላገኙ ስለሆነ በዚህ ተግባር ላይ አትኩሮ መስራት ያስፈልጋል፡፡
በመሆኑም ትምህርት ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ለበርካታ አመታት በአገሪቱ ውስጥ ተበታትኖ ሲሰጥ የቆየውን የልዩ ፍላጎት ትምህርት ሥርዓት ባለውና በተጠናከረ መልኩ ለመስጠት ይቻል ዘንድ በ1998 ዓ.ም የመጀመሪያውን የልዩ ፍላጎት ትምህርት ስትራቴጂ አዘጋጅቷል፡፡ ስትራቴጂውም በውስጡ ያሉትን ክፍተቶች ለመሙላት፣ በትግበራ ወቅት ላጋጠሙ ችግሮች መፍትሄ ለመስጠትና ከወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር ለማጣጣም ሲባል በ2004 ዓ.ም ተከልሷል፡፡
መንግስት ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ትምህርትን ለሁሉም ዜጎች ለማዳረስ ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡የትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት መረጃ ሥርዓት (EMIS) እንደሚያመለክተው በ1999 የመጀመሪያ ደረጃ የትም/ እድል ያገኙት ልዩ ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎች ብዛት 33,300 የነበረ ሲሆን ይህ ቁጥር በ2007 ዓም 71,007 ደርሷል፡፡ በእነዚህ አመታት አንጻራዊ የቁጥር መጨመር ቢታይም ልዩ ፍላጎት ያላቸው በተለይም የአካል ጉዳተኛ ዜጎች የትምህርት ተደራሽነት አሁንም በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ለአብነት ያህል ለመጥቀስ በ2007 ዓም በመጀመሪያ ደረጃ የትምህርት እድል ማግኘት ያለባቸው አካል ጉዳተኛ ህጻናት ብዛት ወደ 1.86 ሚሊዮን የሚገመት ሲሆን በትምህርት ገበታ ላይ የነበሩት ግን 71,007 (3.8%) ብቻ ናቸው፡፡ይህም ሁኔታ በአጠቃላይ ልዩ ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎች የትምህርት አገልግሎቱ ተጠቃሚ አለመሆናቸውን ያመለክታል፡፡
1. የትምህርት ቤቶች የድጎማ በጀት
የትምህርት ቤቶች ድጎማ በጀት በኢትዮጵያ መንግስትና በልማት አጋሮች በተነደፈው ሁለተኛው ምዕራፍ የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፕሮግራም ሥር የሚተዳደር ሆኖ በሁሉም የመንግስት የ“ኦ ክፍል”፣ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም በአማራጭ መሠረታዊ ትምህርት መስጫ ማዕከላት ዘንድ የትምህርት አሠጣጥ አፈፃፀም ብቃት ለማጎልበትና የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የተነደፈ መርሃ ግብር ነው፡፡
የትምህርት ቤቶች ድጎማ በጀት ትምህርት ቤቶች በሚኖሩዋቸው ተማሪዎች ብዛት መሠረት በአገሪቱ ለሚገኙ ሁሉም በመንግስት የቅድመ መደበኛ፣ የአማራጭ መሠረታዊ ትምህርት ማዕከላት ፣ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚመደብ ገንዘብ ነው፡፡
የትምህርት ቤቶች ድጎማ በጀት ለመማር እና ማስተማር ተግባራት መሻሻል ልዩ ትኩረት በመስጠት በወላጅ ተማሪ መምህር ህብረት (ወ.ተ.መ.ህ.) ወሳኝነት ትምህርት ቤቶች የትምህርት ቤት መሻሻል ዕቅዶቻቸውን ለመተግበርና የአፈፃፀም ብቃታቸውን ለማሻሻል የሚጠቀሙበት ገንዘብ ነው፡፡
በሁለተኛው ምዕራፍ የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፕሮግራም የፕሮጀክት ስምምነት ሰነድ ለመማር እና ማስተማር ተግባራት ልዩ ትኩረት የተሰጠው ሲሆን በዚሁ መሰረት ትም/ቤቶች ከሚመደብላቸው የድጎማ በጀት ውስጥ ቢያንስ 50% ያህል በትምህርት ቤት መሻሻል ዕቅዶቻቸው ለመማርና ማስተማር ርዕሰ ጉዳዮች መጠቀም ይኖርባቸዋል፡፡የትምህርት ቤቶች የድጎማ በጀት አመዳደብ ከትምህርት ሥራ አመራር መረጃ ሥርዓት (EMIS) በተገኘ የተማሪዎች ምዝገባ መረጃ ላይ ተመርኩዞ የሚደለደል/የሚፈፀም ነው፡፡
የትምህርት ቤት ድጎማ በጀት ወላጆችና ህብረተሰቡ ለትምህርት ቤቶችና የአማራጭ መሰረታዊ ትምህርት ማዕከላት በየዓመቱ ለሚሰጡት የገንዘብ ድጋፍ ማሟያ የሚሆን እንጂ የነበረውን አሰራር ወይም በመንግስት ለትምህርት ቤቶች የሚመደበውን በጀት የሚተካ አይደለም፡፡ የትምህርት ቤት ድጎማ በጀት ት/ቤቶች የመማር ማስተማሩን ሥራ/ሁኔታ ለማሻሻል እንዲረዳቸው የሚመደብ ተጨማሪ ገንዘብ ነው፡፡
የት/ቤት መሻሻል ዕቅዶች በተጨባጭ ማስረጃ ላይ የተመሠረቱ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ የወላጆች፣ የተማሪዎችና የመምህራን ህብረቶች የየት/ቤቶቻቸውን ዕቅዶች ሲያዘጋጁ የመማርና ማስተማር ተግባሩን ውጤታማ ለማድረግ የሚረዱ ተግባራትን ለመለየት እንዲያስችላቸው የሁሉም ትምህርት ዓይነቶች የተማሪዎች ውጤት፣ የተማሪዎች በክፍል ውስጥ መኖርና አለመኖር፣ የተማሪዎች በክፍል መድገምና ማቋረጥ መጠን፣ የመማሪያና ማስተማሪያ ቁሳቁሶች አቅርቦት፣ እንዲሁም ከመምህራንና ከተማሪዎች የሚሰበሰቡ ከመማርና ማስተማር መስተጋብር ጋር አግባብነት ያላቸውን መረጃዎች መጠቀም ይኖርባቸዋል፡፡ በተመሳሳይም ልዩ ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎች በፍላጎታቸው ዓይነት መለየት፣ በመማር ማስተማር ሂደቱ የሚያስመዘግቧቸው ውጤቶች፣ የሚያጋጥሟቸው ችግሮችና የሚደረግላቸው ልዩ ድጋፍን በተመለከተ በመከታተል መረጃ መያዝ ያስፈልጋል።
2. የትምህርት ፍትሀዊነት ለማረጋገጥ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ያለበት ሁኔታ
እ.አ.አ. በ2011 በአለም ጤና ድርጅት (WHO) የተደረገ ጥናት እንደሚጠቅሰው በዓለም ላይ በማንኛውም ማህበረሰብ ካለው ህዝብ ውስጥ 15 በመቶ የሚሆነው ልዩ ፍላጎት ያለው ነው። በመሆኑም በአምስተኛው የትምህርት ዘርፍ ልማት ፕሮግራም እንደተቀመጠው በሀገራችን እድሜያቸው ከ4-18 ዓመት የሆኑ ህጻናት 33.5 ሚሊዮን እንደሆኑና ልዩ ፍላጎት ያላቸው ህጻናት ወደ 5 ሚሊዮን እንደሚገመቱ ተጠቅሷል። በመቀጠልም በ2006 ዓ.ም 77,850 ህጻናት ከ1ኛ-12ኛ ክፍል ባሉ የትምህርት ደረጃዎች በትምህርት ገበታ ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል። በተጨማሪም በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት መማር ከሚገባችው ልዩ ፍላጎት ያላቸው ህጻናት ውስጥ 4 በመቶ ብቻ በመማር መሆናቸውን ያሳያል።
በአምስተኛው የትምህርት ዘርፍ ልማት ፕሮግራም ሰነድ ላይ እንደተዘረዘረው ልዩ ፍላጎት ያላቸው ህጻናትን ወደ ትምህርት ገበታ እንዳይመጡ ከሚያደርጉ ተግዳሮቶች ውስጥ፦
• በልዩ ፍላጎት ትምህርት ላይ የህብረተሰቡ ግንዛቤ አናሳ መሆን
• ከትምህርት ሚኒስቴር እስከ ትምህርት ቤት ድረስ ባሉት መዋቅሮች የትምህርት አመራርሮች በልዩ ፍላጎት ትምህርት ላይ የታቀዱ ተግባራትን ለመተግበር ያላቸው የዕውቀት፣ የክህሎትና የተነሳሽነት ሁኔታ ማነስ
• ልዩ ፍላጎት ያላቸው ህጻናት ያሉበትን ሁኔታ ለማወቅና አመቺና ውጤታማ የሆኑ ስልቶችን ለመንደፍ ተዓማኒነት ያለው መረጃ ዕጥረት
• ከፈደራል እስከ ወረዳና ት/ቤት ድረስ ባለው የትምህርት መዋቅር የልዩ ፍላጎት ትምህርትና ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮች ዙርያ በቅንጅትና በትብብር ሊያሰራ የሚችል ግልጽ የሆነ መዋቅርና የአሰራር ስርዓት አለመኖር
• የልዩ ፍላጎትና አካቶ ትምህርትን ለመደገፍ የሚያስችል የፋይናንስ ድጋፍና አሰራር ያለመኖር
• የት/ቤቶች መሰረተ ልማትና የአገልግሎት መሳሪያዎች ደካማ መሆን፣ ለልዩ ፍላጎት ትምህርት የተዘጋጀ የመማር ማስተማር ስልት ያለመኖር፣ እንዲሁም ተያያዥ የሆኑ መመሪያዎችና ስታንዳርዶች ያለመኖር
• የልዩ ፍላጎት ትምህርት መምህራን የማስተማር ክህሎት ጠንካራ ያለመሆን
• በልዩ ፍላጎት የሪሶርስ ማዕከላትና በሳተላይት ትምህርት ቤቶች ለሚሰሩ ተዘዋዋሪ መምህራንን ለመደገፍ የተዘረጋ የደረጃ ዕድገት ስርዓት ያለመኖር ተጠቃሽ ናቸው።
3. ልዩ ፍላጎት ላላቸው ህፃናት የተመደበ ተጨማሪ የት/ቤቶች ድጎማ በጀት
ልዩ ፍላጉት ያላቸውን ህፃናት በትምህርት ድጋፍ ለማድረግና አመቺ የትምህርት አካባቢ እንዲኖራቸው ለመርዳት እንዲሁም የት/ቤቶች መገልገያዎች ለእነዚህ ህፃናት አመቺ እንዲሆኑ ለማድረግ ከትምህርት አመራር መረጃ ስርዓት በተገኘ መረጃ መነሻነት በ2008 በጀት ዓመት ክልሎች ከሚደርሳችው ጠቅላላ በጀት አንድ በመቶ ለልዩ ፍላጎት ተማሪዎች እንዲውል ተመድቦ የነበረ ሲሆን ክልሎች በክልላቸው ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ተግባራዊ ሲያደርጉ ቆይተዋል። በዚህም መሰረት በት/ቤት መሻሻል ፕሮግራም አተገባበርና በት/ቤት ድጎማ በጀት አጠቃቀም ላይ በተከናወነ ጥናት እንዲሁም ከልማት አጋሮች ጋር በመተባበር በተከናወነ የጋራ ግምገማና ክልላዊ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት በአንዳንድ ክልሎች በመመሪያው መሰረት ልዩ ፍላጎት ያላቸው ት/ቤቶችንና የተማሪዎችን ቁጥር በመለየት ባለድርሻዎችን በማሳተፍ ለተማሪዎቹ አስፈላጊ የትምህርት መሳሪዎች በመግዛት ተማሪዎቹ እንዲጠቀሙባቸው አድርገዋል። በሌላ በኩል አንዳንድ ክልሎችና ወረዳዎች ከመመሪያው ውጪ ለተማሪዎች ቀጥታ የኪስ ገንዘብ የሰጡበት ሁኔታ ታይቷል።
በመሆኑም ውጤታማ በሆነ መልኩ ያከናወኑ ክልሎችና ወረዳዎችን ልምድ በመውሰድ ልዩ ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎች ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ በ2009 በጀት ዓመት ለሁሉም ክልሎች ተጨማሪ 2% የት/ቤቶች ድጎማ በጀት እንዲመደብ ተደርጓል፡፡
4. ለልዩ ፍላጎት ትምህርት አገልግሎት የተመደበውን የትምህርት ቤት ድጎማ በጀት አጠቃቀምን በሚመለከት በየደረጃው መከናወን ያለባቸው ተግባራትና ሀላፊነቶች
የክልል ትምህርት ቢሮዎች፣ የወረዳ ትምህርት ጽ/ቤቶችና ት/ቤቶች ለልዩ ፍላጎት ትምህርት አገልግሎት የተመደበውን የትምህርት ቤት ድጎማ በጀት አጠቃቀም በሚመለከት የሚጠበቅባቸውን ሀላፊነትና ተግባራት ተገንዝበው በጀቱን በመመሪያው መሰረት ተማሪዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በሚያደርግ መልኩ ስራ ላይ እንዲውል ድጋፍና ክትትል እንዲያደርጉ ተግባራትና ሀላፊነቶቻቸው በሚከተለው መልኩ ቀርበዋል።
4.1 የክልል/ ከተማ መስተዳድር ትምህርት ቢሮ ተግባራትና ሀላፊነቶች
• ከት/ቤት ጀምሮ እስከ ክልል ያሉ አካላት የልዩ ፍላጎት ተማሪዎችን ቁጥርና አይነት ለይተው በማጠናቀር ለክልሉ እንዲያቀርቡ ማድረግ
• የልዩ ፍላጎት ትምህርት ድጎማ በጀት በስራ ላይ ለሚያወሉ ወረዳዎች፣ ት/ቤቶችና ኮሚቴዎች ስለአጠቃቀሙ ግንዛቤ መፍጠሪያ ስልጠና መስጠት
• የልዩ ፍላጎት ተማሪዎችን ቁጥር መሰረት በማድረግ ለክልሉ/ከተማ መስተዳድሩ የተመደበውን በጀት በመደልደልና በማሰራጨት ለት/ቤቶች በወቅቱ አንዲደርስን ለዚሁ አገልግሎት እንዲውል እንዲደርስ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ
• ለልዩ ፍላጎት ተማሪዎች አገልግሎት የተገዙ ቁሳቁሶች ት/ቤት መድረሳቸውንና ስራ ላይ መዋላቸውን በመከታተል ድጋፍ መስጠት
• የልዩ ፍላጎት ትምህርት ድጎማ በጀት አጠቃቀምን በተመለከተ ወረዳዎች ሪፖርት እንዲያቀርቡ በማድረግ ግብረ-መልስ መስጠት
• ከክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ጋር በመተባበር ከክልሉ ናሙና ት/ቤቶችን በመውሰድ ስለአጠቃቀሙ ዳሰሳ በማድረግ ግብረ-መልስ መስጠት
• በማዕከል ደረጃ ለሚከናወን ትምህርት ድጎማ በጀት አጠቃቀም ኦዲት በተለይ በጀቱ ለታቀደለት የልዩ ፍላጎት ትምህርት አገልግሎት መዋሉን ከማረጋገጥ አንጻር ድጋፍ መስጠት
4.2 የወረዳ/ዞን/ልዩ ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ተግባራትና ሀላፊነቶች
• ት/ቤቶች የልዩ ፍላጎት ተማሪዎችን መረጃ በቁጥርና በአይነት ለይተው መረጃውን በማጠናቀር ለወረዳ እንዲልኩ ክትትል ማድረግ
• ከክልሉ የተመደበው በጀት ለት/ቤቶች በወቅቱ እንዲደርስ ድጋፍና ክትትል ማድረግ
• ት/ቤቶች የተመደበላቸው ገንዘብ የሚመለከታቸውን አካላት በማሳተፍ የትምህርት መሳሪያዎችን በመግዛት የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች ተጠቃሚ ማድረጋቸውን መከታተል
• የልዩ ፍላጎት ትምህርት ድጎማ በጀት አጠቃቀምን በተመለከተ ት/ቤቶች ሪፖርት እንዲያቀርቡ በማድረግ ግብረ-መልስ መስጠት
• ከወረዳው ፋይናንስና ኢኮኖሚ ትብብር ጽ/ቤት ጋር በመተባበር በት/ቤቶች በመገኘት የልዩ ፍላጎት ትምህርት ድጎማ በጀት አጠቃቀምን በተመለከተ ኦዲት በማከናወን ሪፖርት ማጠናቀርና ግብረ-መልስ መስጠት
• የልዩ ፍላጎት ትምህርት ድጎማ በጀት አጠቃቀም በተመለከተ መደራጀት ያለባቸውን መረጃዎችና ሰነዶች አሟልተው እንዲይዙ ድጋፍና ክትትል ማድረግ
• በማዕከል ደረጃ ለሚከናወን የልዩ ፍላጎት ትምህርት ድጎማ በጀት አጠቃቀም ኦዲት ድጋፍ መስጠት
4.3 የት/ቤት ተግባራትና ሀላፊነቶች
• ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍና የልዩ ፍላጎት ተማሪዎችን ቁጥርና ፍላጎት፣ የአጠቃቀም መመሪያ እና የተመደበውን በጀት መሰረት በማድረግ የልዩ ፍላጎት ትምህርት በጀት አጠቃቀም ዕቅድ ማዘጋጀት
• በተዘጋጀው ዕቅድ መሰረትና ከወላጅ ተማሪ መምህር ህብረት /ወተመህ/ ጋር በመሆን የተመደበውን በጀት በወቅቱ ስራ ላይ እንዲውል ማድረግ
• ለልዩ ፍላጎት ተማሪዎች አገልግሎት የተገዙ የት/ቁሳቁሶች ባግባቡ እንዲጠቀሙ ሁኔታዎችን ማመቻቸት
• ለልዩ ፍላጎት ተማሪዎች ተጨማሪ ድጋፍ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት የሚገኝበትን ስልት ቀይሶ ተግባራዊ ማድረግ
• ለልዩ ፍላጎት ተማሪዎች የተመደበ በጀት በተመለከተ የማስታወቂያ ሰሌዳ በማዘጋጀትና በሚታይ ቦታ በመለጠፍ ህብረተሰቡ እንዲያውቀው ማድረግ
• የልዩ ፍላጎት ትምህርት ድጎማ በጀት አጠቃቀምን በተመለከተ በየሩብ ዓመቱ ለወረዳ ት/ጽ/ቤት የተሟላ ሪፖርት ማቅረብ
• የልዩ ፍላጎት ትምህርት ድጎማ በጀት አጠቃቀም በተመለከተ መረጃዎችና ሰነዶችን አሟልቶ ባግባቡ አደራጅቶ መያዝ
• በወረዳና በማዕከል ደረጃ ለሚከናወኑ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ድጎማ በጀት አጠቃቀም ኦዲት ድጋፍ መስጠት
5. በGEQIP II የተመደበው 2% የትምህርት ቤት ድጎማ በጀት በመጠቀም ልዩ ፍላጎት ላላቸው ተማሪዎች አገልግሎት የሚሰጡ የትምህርት ቁሳቁሶች
አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች እንደ ጉዳታቸውና ፍላጎታቸው ዓይነት ሊገለገሉባቸው የሚገቡ የትምህርት ቁሳቁሶችና የድጋፍ ሰጪ መሣሪያዎች ያስፈልጓቸዋል፡፡ የትምህርት ተቋማቱ በተቻለ መጠን በተቋም ደረጃ ሊያገለግሉ የሚችሉ ቁሳቁሶችን ቅድሚያ በመስጠትና ልዩ ፍላጎት ያላቸው ህጻናትና ተማሪዎችን ፍላጎት በማጥናት የተመደበውን 2% በጀት በአግባቡ መጠቀም እንዳለባቸው ይታመናል፡፡ ይህንንም በጀት ትምህርት ቤቶች እንደ ተማሪዎቹ ጉዳትና ፍላጎት ዓይነት በውጤታማነት ለመጠቀም እንዲችሉ ቀጥሎ የተዘረዘሩት ቁሳቁሶች ቅድሚያ የሚሰጣቸውን በማስቀደም ቀርበዋል፡-
5.1 ማየት ለተሳናቸው
• ስሌትና ስታይለስ (slate & styles)
• የብሬይል ወረቀት
• አባከስ (የሂሳብ መማሪያ)
• ኬን ( ነጭ በትር)
• የብሬይል ማስመሪያ
• የቃላት መመስረቻ ኪት (kit)
• የስሌት ትምህርት ኪት (kit)
• የብሬይል ሰዓት (Braille watch)
• የሚናገር ሰዓት (talking watch)
• ብሬለር (Brailler) የብሬል ጽህፈት መሳሪያ
• የሚናገር የስሌት መሳሪያ (calculator)
• ኮምፒዩተር (with JAWS)
• አጉሊ መነፅር
• የማንበቢያ ቋሚ (reading stand) ፤
• በትላልቁ የተፃፉ መማሪያዎች (large print books) ለጭላንጭሎች
• የሚዳሰሱ ካርታዎች (tactile maps)
• የማድመጫ መሳሪያ ( head phone)
• ባለድምፅ ኳስ(sound ball)
5.2 መስማት ለተሳናቸው
• የጆሮ ማድመጫ መሳሪያ (hearing aids)
• የምልክት ቋንቋ መዝገበ ቃላት
• የምልክት ቋንቋ ቻርት
• የጆሮ ማድመጫ መሳሪያ (hearing aids)
• ኦቶስኮፒ (otoscopy)
• ኦዲዮሜትር (Audiometer)
5.3 የአካላዊ እንቅስቃሴ ችግር ላለባቸው (Physical impairment) ህጻናትና ተማሪዎች
• ተሸከርካሪ ወንበሮች
• ክራች (crutch)
• መራመጃ መሳሪያዎች (xxxxxx)
• መተላለፊያዎችን(Ramp)ለምሳሌ ወደ መማሪያ ክፍሎች፣ ቤተ-መፃህፍት ቢሮዎች፣መፀዳጃ ቦታዎች፣ የሚወስዱ መተላለፊያዎችን መስራት
• በኮሪደሮችና በመፀዳጃ ቤቶች የሚያገለግሉ የእጅ መደገፊያዎች (Hand rails),
• አካላዊ ጉዳት ላለባቸው ተማሪዎች አገልግሎት የሚሰጡ የተመቻቹ የመፀዳጃ ቤቶች (adapted toilets)፣ የውሃ ቧንቧ፣ቤተ-መጻህፍት፣ቤተ-ሙከራዎች
5.4 የዓዕምሮ ዕድገት ውስንነት ላለባቸው ህጻናትና ተማሪዎች
• የተለያዩ የሞንቴሶሪ ኪትስ (kits)
• ቴሌቪዥንና ዲቪዲ
• እራስን ችሎ ህይወትን ለመምራት የሚያስችል ክሂል መማሪያ አጋዥ የሚሆኑ ማጣቀሻ መፃህፍት
o መማሪያ መፃህፍት
o የሙያና ቴክኒክ ስልጠና ቁሳቁሶች ናቸው፡፡
5.5 የንግግርና የተግባቦት ችግር ላለባቸው ህጻናትና ተማሪዎች
• የንግግር ችግር ላለባቸው ልጆች አገልግሎት ሊሰጥ የሚችል የንግግር ስልጠና ኪት (kit) መስታወትን የጨምራል፣
• በስዕላዊ መረጃ የመግባቢያ ዘዴ መጠቀሚያ (PECS)
5.6 የድጋፍ መስጫ ማእከላትን ማቋቋም
የልዩ ፍላጎት/አካቶ ትምህርት የድጋፍ መስጫ ማዕከላትን ማቋቋም
• በልዩ ትምህርት ቤትም ሆነ በአካባቢያቸው አካተው በሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለሚገኙ ሁሉም ተማሪዎች (ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ተማሪዎች ጨምሮ) ተገቢው ዕገዛ ይደረግ ዘንድ አስፈላጊውን የማስተማር ልምድና ሙያዊ ድጋፍ መስጠት
• ለሁሉም ተማሪዎች ማለትም ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ተማሪዎች ጨምሮ የመማር ክሂላቸው እየዳበረ ይሄድ ዘንድ ተገቢውን የምክርና የጤና አገልግሎት የሚያገኙበትን ሁኔታዎች ማመቻቸት
• ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ተማሪዎች የትምህርት ተሳትፎ ይበልጥ ለማሳደግ አስፈላጊውን የትምህርት ግብዓቶች፤ ቁሳቁሶችና የአካል ድጋፍ መርጃ መሳሪያዎች (የዓይን መነፅር፤የማድመጫ መሳሪያ ፤ የመረማመጃ መሳሪያ ወዘተ) ማሟላት
• ሁሉም ተማሪዎች ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ጨምሮ ወደ ትምህርት ገበታ ማምጣት ይችሉ ዘንድ አጎራባች ትምህርት ቤቶችን በስልጠና ማገዝ፤ የትምህርት ግብዓቶችን
የማዋስ፤ ለህክምና ወደ ሆስፒታል መላክ፤ የተማሪዎችን ችግር የመለየትና የመዳሰስ ተግባር እንዲከናወን ተገቢውን ድጋፍ መስጠት
• ለተገቢው ዕገዛና ትብብር በአካባቢው ከሚገኙ ወላጆች፤ ትምህርት ቤቶች፤ ክሊኒኮች፤ የወረዳ የትምህርት ጽ/ቤትና መያዶች ጋር በጋራ መስራት የሚያስችል መረብ መፍጠር
• በድጋፍ መስጫ ማዕከሉ በተቋቋመው ኮር ቲምና በመምህራን ትብብር የተመሰረተ ትምህርት ቤት-ዐቀፍ የዳሰሳ፤ የመለያና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ለምርመራ ወደ ሆስፒታል መላክና ከሆስፒታሎች ጋር በትብብር የመስራት ሁኔታዎችን ማደራጀት ናቸው፡፡
• አካላዊ ጉዳት ላለባቸው ተማሪዎች አገልግሎት የሚሰጡ የተመቻቹ የመፀዳጃ ቤቶች (adapted toilets)፣
• በየክፍል መግቢያው መተላለፊያዎች (ramps/፣
• ከክፍል ወደ ክፍልና ከህንጻ ወደ ህንጻ መተላለፊያዎች፣
• መፀዳጃ ቤቶችን እንደ አካል ጉዳታቸው እንዲጠቀሙ፣
• ከውሃ ቧንቧ እንደ ጉዳታቸው ዓይነት መጠጣት እንዲችሉ፣
• በቤተ መጻህፍት እንደ ጉዳታቸው ዓይነት መጠቀም እንዲችሉ፣
• በቤተሙከራዎችና በሌሎችም እንደ ጉዳታቸው ዓይነት መጠቀም እንዲችሉ በየትምህርት ተቋማቱ ግብዓቶች ሊሟሉላቸው ይገባል፡፡
6. ማህበረሰቡ በት/ቤቶች ድጎማ በጀት አጠቃቀም ላይ ክትትል እንዲያደርግና ተጠያቂነት እንዲኖር የሚያስችል የአሠራር ዘዴ
ማህበረሰቡ በትምህርት ቤቶች አሰራር ላይ ያለው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት የአካባቢው ማህበረሰብ በትምህርት ቤቶች የትምህርት ቤት ድጎማ በጀት አስተቃቀድና አጠቃቀም ላይ ቁልፍ ድርሻ እንዲኖረው ተደርጎ በአተገባበር መመሪያው በግልጽ ተቀምጧል። ከዚህ አንጻር፦
• በትምህርት ሚኒስቴርና እና በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ለክልሎች የተላከውን ጠቅላላ የገንዘብ መጠን እንዲሁም ለእያንዳንዱ ክልልና ወረዳ የሚከፋፈለውን የገንዘብ መጠን የሚያሳዩ ደብዳቤዎች ቅጂዎች በግልጽ
እንዲቀመጡና ለህብረተሰቡ በሚታዩበት አግባብ ለዚሁ በተዘጋጀው የማስታወቂያ ቦርድ እንዲለጠፉ ማድረግ መኖር፡፡
• ሁሉም ትምህርት ቤቶች . በየዓመቱ ጥቅምት 21 (እ.ኤ.አ. ኦክቶበር 31) ላይ የድጎማ በጀታቸውን እነዲያገኙ ማድረግና መከታተል
• ወረዳዎች ልዩ ፍላጎት ላላቸው ተማሪዎች የሚያስፈልጉ የትምህርት መሣሪያዎችን በማሟላት ድጋፍ ማድረግ እንዲችሉ ተብሉ የተመደበውን ተጨማሪ የትምህርት ቤቶች ድጎማ በጀት እንዲደርሳቸው ማድረግ፡፡
• የት/ቤቶች የድጎማ በጀት አመዳደብ፣ አአጠቃቀም ላይ ክትትልና ግምገማ ማካሄድ/የክልል ትምህርት ቢሮዎች እና የፋይናንስና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮዎች በትምህርት ሚኒስቴር የተመደበውን የት/ቤቶች ድጎማ በጀት መጠን ትክክለኛነት ማረጋገጥ፡፡
• የክልል ትምህርት ቢሮዎች ልዩ ፍላጎት ላላቸው ተማሪዎች ትምህርት ማጠናከሪያ የተላከው 2% ተጨማሪ የት/ቤቶች ድጎማ ተማሪዎቹ የሚገኙባቸውን ወረዳዎችና ት/ቤቶች ባላቸው ዕውቀት/መረጃ መሠረት በመለየት ገንዘቡ ደርሶ በተገቢው ሥራ ላይ እንዲውል ማድረግ፡፡
• ልዩ ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎች ያሉዋቸው ወረዳዎች ከሌሎች ወረዳዎች በተለየ ሁኔታ ልዩ ትኩረትና ድጋፍ ይደረግላቸዋል፡፡ በተመሳሳይ መንገድ ወረዳዎቹ ለዚሁ ጉዳይ የተመደበው የድጎማ በጀት የተመዘገቡ ልዩ የትምህርት ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎችን ብዛት መሠረት በማድረግ ተማሪዎቹ ለሚገኙባቸው ት/ቤቶች መላክ ይኖርባቸዋል፡፡
• ከዚህ በተጨማሪ የክልል ትምህርት ቢሮዎች አካታች የሆነ የትምህርት አሰጣጥ ስርዓት ለማጠናከርና ልዩ ፍላጎት ላላቸው ተማሪዎች የሚያስፈልጉ የትምህርት መሣሪያዎች አቅርቦትን ለማሻሻል በሚረዳ መልኩ ገንዘቡን ለሁሉም ወረዳዎች የማዳረስ ነፃነት/መብት አላቸው፡፡
• የክልል ትምህርት ቢሮዎች ልዩ ፍላጎት ላላቸው ተማሪዎች የሚመደበው ተጨማሪ ገንዘብ ለምን ተግባር ማዋል እንደሚገባ ከወሰኑ በኋላ ገንዘቡ ለእያንዳንዱ ወረዳ የተደለደለበት አሠራር፣ ተግባርና የገንዘብ መጠን መረጃ/ሰነዶች አደራጅተው ማስቀመጥ ይገባቸዋል፡፡
• የክልል ትምህርት እና የፋይናንስና ኢኮኖሚ ትብበር ቢሮዎች ልዩ ፍላጎት ላላቸው ህፃናት የተመደበውን ገንዘብ ወረዳዎች ዘንድ በወቅቱ መድረሱን የሚያረጋግጥ ሰነድ አደራጅተው መያዝ ይጠበቅባቸውል።፡፡
7. የትምህርት ቤቶች የገንዘብ አጠቃቀም ግምገማ
በየዓመቱ በሀገሪቱ ካሉ የ” ኦ ክፍል”፣ አማራጭ መሰረታዊ ትምህርት ማዕከላትና መደበኛ ት/ቤቶች 3 በመቶ (3%) ያህሉን በናሙናነት በመውሰድ የተመደበው የድጎማ በጀት በተገቢው ሥራ ላይ መዋሉን ለማረጋገጥና ቁጥጥር ለማድረግ እንዲረዳ የሒሳብ ምርመራ ይካሄዳል፡፡