Contract
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት እና በቱርክ ሪፐብሊክ መንግስት መካከል የተደረገውን በወንጀል ጉዳዮች የጋራ የሕግ ትብብር ስምምነት ለማፀደቅ የተዘጋጀ ማብራሪያ (መግለጫ)
ሕዳር 2015 ዓ.ም
1. መግቢያ
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት እና በቱርክ ሪፐብሊክ መንግስት መካከል እ.ኤ.አ. ሜይ 10 ቀን 2022 በወንጀል ጉዳዮች የጋራ የህግ ትብብር ስምምነት በአንካራ (ቱርክ) ተፈርሟል።
በስምምነቱ መግቢያ ላይ ስምምነቱ በወንጀል ምርመራ፣ ክስ እና የክርክር ሂደት የሁለቱንም ሀገራት የህግ አካላት ዉጤታማ በማድረግ የወንጀል መከላከል ስራን ዉጤታማነት ለማሳደግ እንዲሁም የሀገራቱን ሉዓላዊነት፣ የእኩልነት እና አንዱ በሌላዉ ዉስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ ያለመግባት መርሆዎችን መሰረት በማድረግ የሀገራቱን የቆየ መልካም ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እና በወንጀል ጉዳዮች የጋራ የህግ ትብብርን በተደራጀ ሁኔታ ለመምራት ታስቦ የተፈረመ ስምምነት መሆኑን ይገልፃል፡፡
ስለሆነም ስምምነቱ በወንጀል ጉዳይ የሚደረግ ምርመራን እና ክስ ሂደትን በሚመለከት ለሚደረገው የሁለትዮሽ ትብብር የሕግ ማዕቀፍን የሚፈጥር በመሆኑ በሚኒስትሮች ምክር ቤት እና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውይይት ተደርጎበት እንዲጸድቅ ለማስቻል ይህ መግለጫ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡
2. ስምምነቱ በአገራችን ላይ የሚጥለዉ ግዴታ
ስምምነቱ በወንጀል ጉዳዮች የጋራ የህግ ትብብር ስምምነት እንደመሆኑ በአገራችን ላይ የሚጥላቸው ልዩ ልዩ ግዴታዎች አሉ። ከእነዚህ መካከልም ዋነኛው በቱርክ ሪፐብሊክ መንግስት በሚቀርብ የትብብር ጥያቄ መሠረት ስምምነቱን እና ሀገራችን ህግን መሰረት በማድረግ በወንጀል ምርመራ፣ ክስ እና የክርክር ሂደት ላይ ባሉ ጉዳዮች ሚፈለጉ ማስረጃዎችን እና መረጃዎችን የመስጠት እንዲሁም ለወንጀል መፈፀሚያነት የዋሉ፣ ሊዉሉ የታሰቡ ወይም የወንጀል ፍሬ የሆኑ ንብረቶችን የመያዝ፣ የማገድ እና የመዉረስ ግዴታ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ ትብብሩን ለማድረግ የሚወጣው ወጪ በአገራችን በኩል እንዲሸፈን ግዴታን ይጥላል። ነገር ግን ትብብሩን ለማድረግ የሚያስፈልገዉ ወጭ መደበኛ ከሆነዉ ወጭ የተለየ እና ትብብር አድራጊ ሀገርን ከፍተኛ ወጭ የሚያስወጣ ከሆነ ወጭዉን ትብብር ጠያቂ ሀገር እንዲሸፍን ማድረግ የሚቻል መሆኑ ተደንግጓል፡፡
ሆኖም በአጠቃላይ የትብብር ስምምነቱ ተፈጻሚነት በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ በሀገራችን በኩል በቱርክ መንግስት የሚቀርብ ጥያቄ የሚስተናገደው በቱርክ መንግስት የሚቀርብን ጥያቄ ሀገራችን በምታስተናግድበት አግባብ ይሆናል።
3. የስምምነቱ መጽደቅ ለአገራችን የሚኖረዉ ጠቀሜታ
ሀገራችን የጀመረችውን የልማት እና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አጠናክሮ ለማስቀጠል ጉልህ ሚና ከሚጫወቱ ነገሮች መካከል የሕግ የበላይነት መከበር ነው፡፡ የዚህም አንዱ መገለጫ የተለያዩ የወንጀል መረጃዎች/ማስረጃዎች በመለዋወጥ ወንጀለኞች ከቅጣት የማያመልጡበትን ሁኔታ መፍጠር ሲሆን ይህንንም ለማከናወን በእንካ ለእንካ (Principle of Reciprocity) ከሚካሄዱ ትብብሮች ባለፈ በሀገራት መካከል ስምምነቶችን መፈራረም እና ፀድቀው ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረግ ዋናው መሳሪያ ነው፡፡
ቱርክ እና ኢትዮጵያ ያላቸዉ ግንኙነት ለረጅም ጊዜ የነበረ እና በተለይም ደግሞ በአሁኑ ሰዓት ዘርፈ ብዙ እና ከዕለት ወደ ዕለት እያደገ መምጣቱ ይታወቃል፡፡ በተለይም በ ንግድ እና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ያላቸዉ ግንኙነት እየጨመረ የመጣ በመሆኑ እና በዚህም ምክንያት ኢትጵያውያን በቀላሉ ወደ ቱርክ መጓዝ መቻላቸው ወንጀል ክስ፣ ምርመራ እና ክስ ሂደት የሚያስፈልጉ መረጃ እና ማስረጃዎች እንዲሁም ለወንጀል መፈፀሚያነት የዋሉ፣ ሊዉሉ የታሰቡ ወይም የወንጀል ፍሬ የሆኑ ንብረቶች ሊሸሹ የሚችሉበት ዕድል ከፍተኛ ነዉ፡፡ በመሆኑም እነዚህን ጉዳዮች በተመለከተ ለሚደረጉትብብሮች በሕግ ማዕቀፍ ምላሽ ለማሰጠት ስምምነቱ አስፈላጊ ነዉ፡፡
4. የስምምነቱ አፈጻጸም
የስምምነቱን አፈጻጸም በሚመለከት የተቀመጡትን ድንጋጌዎች ለማስፈጸምና ተፈጻሚነታቸውን ለመከታተል ኃላፊነቱን የሚወስድ መንግስታዊ አካል መሰየም አስፈላጊ መሆኑ ይታወቃል። ከዚህ አንፃር የስምምነቱ ይዘት በወንጀል ጉዳዮች የሚደረግ የጋራ ህግ ትብብርን የሚመለከት በመሆኑ የወንጀል ጉዳዮች ትብብር አካልነዉ ። በዚህ ረገድ የፌዴራል አስፈፃሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣዉ አዋጅ ቁጥር 1263 አንቀጽ 40(1) እና የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግን ለማቋቋም የወጣው አዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀጽ 6 (12) መሠረት የኢፌዴሪ ፍትሕ ሚኒስቴር በወንጀልና በፍትሐብሔር ጉዳዮች ዓለም አቀፍ ግንኙነትና ትብብር እንዲያደርግ ኃላፊነት የተጣለበት በመሆኑ እንዲሁም በስምምነቱ አንቀጽ 1 መሠረት
የስምምነቱን አተገባበር ለመከታተል የፍትሕ ሚኒስቴር እንደ ማዕከላዊ ባለስልጣን የተሰየመ በመሆኑ ይህንን ስምምነት ለማስፈጸምና ተፈፃሚነቱን ለመከታተል የፍትሕ ሚኒስቴር ኃላፊነት ይኖረዋል፡፡
5. የስምምነቱ ይዘት
ስምምነቱ በይዘት የትብብር ጥያቄዉ ማዕከላዊ ባለስልጣናት፣ የጋራ የህግ ትብብሩ ወሰን፣ የትብብር ጥያቄዉ ፎረም እና ይዘት፣ የትብብሩ አፈጻፀም፣ ጊዜያዊ እርምጃዎች፣የትብብር ጥያቄዉ ውድቅ ሊደረግ ስለሚችልባቸዉ ሁኔታዎች፣ የተለያዩ የትብብር ዓይነቶች ስለሚስተናገዱባቸዉ ሥነ-ሥርዓት እንዲሁም ሌሎች ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችን የያዙ ሃያ አንድ
(21) አንቀጾች አሉት።
በስምምነቱ አንቀጽ 1 በሀገራችን በኩል የፍትሕ ሚኒስቴር እንዲሁም በቱርክ በኩልም የፍትሕ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ማዕከላዊ ባለስልጣን (central Authorities) እንዲሆኑ ተሰይመዋል፡፡ በስምምነቱ አንቀጽ 2 መሰረት ሁለቱ ሀገራት በወንጀል ጉዳች የጋራ የፍትህ ትብብር ለማድረግ ግዴታ የገቡ ሲሆን የጋራ ትብብሩ ወሰን፤
• መጥሪያ ማድረስን፣
• በሁለቱም ሀገራት ህግ ወንጀል በሆኑ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ብርበራ፣ንብረት ማገድ እና መዉረስን፤
• የወንጀል ስፍራ ምርመራን፣ የባለሙያ ምርመራን ፣
• ተጠርጣሪን ቃል መቀበል፣ ምስክር ቃል መቀበል፣ የወንጀል አቤቱታን መቀበል፣
• የወንጀል ሪከርድ መለዋወትን፣
• ለምርመራ የሚያግዙ መረጃዎችንና ሰነዶችን መለዋወጥ፣
• በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን ማፈላለግ እና ሌሎች ተመሳሳይ የሆኑ ትብበሮችንየሚያካትት ነዉ፡፡
በዚሁ አንቀጽ (2) መሰረት ብርበራ፣ንብረት ማገድ እና መዉረስን የሚመለከት ካልሆነ በቀር ትብብሩን ለማድረግ ትብብር የተጠየቀበት ድርጊት በሁለቱ ሀገራት ህግ መሰረት ወንጀል መሆን (Dual Criminality) አስፈላጊ መስፈርት አይደለም፡፡
የትብብር ጥያቄ በፅሑፍ ሊቀርብ እንደሚገባ፤ነገር ግን አስቸኳይ ሁኔታ ሲያጋጥም በኤሌክትሮኒክ መንገድ ሊላክ እንደሚችልና በሰላሳ ቀን ዉስጥ በፅሁፍ ከነማስረጃዎቹ ሊላክ እንደሚገባ ይገባል፡፡
ከትብብር ጥያቄው ጋር ተያያዘው ሊቀርቡ የሚገባቸው ሰነዶች በስምምነቱ አንቀፅ 3 ላይ የተዘረዘሩ ሲሆን እነዚህ ሰነዶችም የሚከተሉት መረጃዎች የሚያሳዩ ሊሆኑ ይገባል፡-
• ጥያቄውያቀረበው እና የቀረበለት የመንግስት አካል
• ምርመራ እተደረገበት ያለዉ ወይም ክስ የቀረበበት አካል
• መረጃ አለበት የተባለዉን ሰዉ እና ተጠርጣሪዉን፣ ተከሳሽ ወይም ቅጣት የተወሰነበትን ሰዉ ስም፣ የትዉልድ ጊዜና ቦታ፣ ዜግነት፣ ሙያ፣ የእናትና አባት ስም እንዲሁም ህጋዊ ተወካይ ካለዉ የተወካዩ ሙሉ መረጃ
• የትብብርዓይነቱ፣ ትብሩ የተጠየቀበትን ድርጊትፍሬነገሮችየሚያብራራመረጃ እና ከምርመራውጋርተያያዥነትያለውየወንጀልድንጋጌ፣
• ማስረጃዉ በልዩ ስነ ስርዓት ተሰብስቦ እንዲላክ ከተፈለገ የሚሰበሰብበትስርዓትእና
• ሌሎችእንደ ትብብሩ ዓይነት ትብብሩንውጤታማለማድረግአስፈላጊየሆኑመረጃዎች
• የጠያቂ አካልን ፊርማ እና ማህተም ናቸዉ፡፡
አንድ የቀረበ የትብብር ጥያቄ ከትብበር ተጠያቂ ሀገር ውስጥ ህጎች ጋር እስካልተቃረነ ድረስ በሚመለከተው የመንግስት ተቋም ተግባራዊ ሊደረግ እንደሚገባው እንዲሁም ይህን አስመልክቶ ለጥያቄ አቅራቢ ሀገር ማሳወቅ እንደሚገባ በስምምቱ አንቀፅ 4 ስር ተደንግጓል፡፡ የትብብር ጥያቄው ተግባራዊ ሊደረግ የማይችልበት ምክንያት ካለም ተጠያቂው ሀገር ጥያቄ ላቀረበው ሀገር ይህን በሚመለከት በፍጥነት ማሳወቅ እንዳለበት በተመሳሳይ አንቀጽ ተደንግጓል፡፡ በተጨማሪም እንደ ትብብሩ ዓይነት እና የሀገሪቱ ህግ እስከፈቀደ ድረስ የትብብር ጠያቂ ሀገር ተወካይ ትብብር በሚደረግበት ሀገር ፍርድ ቤት ሂደት ላይ ሊገኝ እንደሚችል ደንግጓል፡፡
አንቀጽ 5 አስቸኳይ ሁኔታ ሲያጋጥም እና ጠያቂ ሀገር ሲያመለክት ጥያቄዉ ከወዲሁ ዉድቅ የተደረገ ካልሆነ በቀር ማስረጃዎቹ ባሉበት ሁኔታ እንዲቆዩ ለማድረና እንዳይሸሹ ለማድረግ ጊዜያዊ እርምጃ በተጠያቂው አገር ሊወሰድ እንደሚችል ይደነግጋል፡፡
አንቀጽ 6 ሰነዶችን ለማድረስ የሚደረግን ትብብር የሚመለከት ሲሆን የትብብር ጠያቂ ሀገር የዉስጥ ህግ በሚፈቅደዉ መሰረት ትብብር የማድረስ ግዴታ ያለበት ሲሆን ትብብር ተጠያቂ ሀገር ሰነዱን ለሚመለከተው ሰው ያስረከበ ስለመሆኑ የሚያሳይ ማረጋገጫ ለትብብር አቅራቢ ሀገር መስጠት ይኖርበታል፡፡
አንቀጽ 7 መረጃ መለዋወጥን የሚመለከት ሲሆን አንድ የስምምነቱ አባል ሀገር እያከናወነ ባለዉ የወንጀል ምርመራበሌላኛዉ አባል ሀገር ምርመራ ለማስጀመር የሚያስችል መረጃ ካገኘ ሌላኛዉ ሀገር ጥያቄ ባያቀርብም መረጃዉን መላክ ወይም ማስተላላፍ እንደሚችል ይደነግጋል፡፡ በአንቀጽ 8 በቀረበ የትብብር ጥያቄ መሰረት የተገኘ ማስረጃ ወይም መረጃ ትብብር ከተደረገበት ዓላማ ውጭ ከትብብር ሰጪ አገር ፈቃድ ውጭ ለሌላ ጉዳይ መጠቀም (restricted use) እንደማይቻል ተደንግጓል፡፡ ነገር ግን ትብብር የተጠየቀበት ጉዳይ በምርመራዉ ሂደት ባህሪዉ በመቀየሩ ምክንያት፣ ተጨማሪ ተጠርጣሪዎች በመካተታቸዉ ምክንያት እና ከድርጊቱ በመነጨ የፍትሐ ብሄር ጉዳይ ላይ መረጃዎቹን እና ማስረጃዎቹን ለመጠቀም ፈቃድ መጠየቅ አያስፈልግም፡፡
አንቀጽ 9 የሰነዶችን ተቀባይነት የሚመለከት ሲሆን ሁለቱ አባል ሀገራት የሚለዋወጧቸዉ ማንኛዉም ሰነዶች መረጋገጥ (Authentication) የማያስፈልጋቸዉ መሆኑ ተደንግጓል፡፡
አንቀጽ 10 ትብብር ያደረገ ሀገር ሆነ ብሎ ካልተወ በቀር ሀገራቱ በትብብሩ አማካኝነት የተለዋወጧቸዉ ሰነዶች እና ንብረቶች የተላለፉበትን ዓላማ ካጠናቀቁ ወደ መጡበት ሀገር ሊመለሱ እንደሚገባ ይደነግጋል፡፡
አንቀጽ 11 የትብብር ጥያቄ ሲቀርብ የጠያቂ ሀገር ዜግነት ያለዉን ሰዉ በተመለከተ በትብብር አድራጊ ሀገር የተመዘገበ የወንጀል ሪከርድ ካለ መረጃዉን በመስጠት ትብብር የማድረግ ግዴታ እንዳለባቸዉ ደነግጋል፡፡
አንቀጽ 12 በትብብር ሰጪ ሀገር ውስጥ የሚገኝ አቤቱታ አቅራቢ፣ምስክር ወይም ባለሙያ በትብብር ጠያቂ ሀገር የፍርድ ሂደት በአካል እንዲቀርብ ሲወሰን እና ይህንኑ ጥያቄ ሲያቀርብ ተጠያቂ ሀገር መጥርያ የማድረስ ግዴታ እንዳለበት እና ለጠያቂ ሀገር ማድረሱን ማሳወቅ እንዳለበት ነገር ግን ግለሰቡ መጥሪያዉን አክብሮ ካቀረበ ሊታሰር እንደማችል፤ ይህንን በሚመለከት ሰዎችን ለማጓጓዝ የሚያስፈልጉ ወጭዎች በጠያቂ ሀገር እንደሚሸፈን፤ እንዲሁም ይህንን መጥሪያ አክብሮ በትብብር ጠያቂ ሀገር የተገኘ ግለሰብ ግለሰቡ ወደ ጥያቄ አቅራቢ ሀገር ከመዘዋወሩ በፊት በፈፀመው የወንጀል ድርጊት ሊጠየቅ እንደማይገባው የተገለጸ ሲሆን ነገር ግን ይህ ዋስትና ግሰለቡ ከጥያቄ አቅራቢ ሀገር ግዛት ውስጥ በ30 ቀናት ውስጥ እንዲወጣ ከተነገረው በኋላ በራሱ ምክንያት ባለመዉጣት በጠያቂ
ሀገር የግዛት ክልል ዉስጥ የተገኘ ከሆነ ሊጠየቅ እንደሚችል እና ጠያቂ ሀገር ዋስትናዉን የማክበር ግዴታ እንደሌለባት ተደንግጓል፡፡
በትብብር አድራጊ ሀገር ውስጥ በእስር የሚገኝ ፍርደኛ ግለሰብ በጊዜያዊነት ወደ ትብብር ጠያቂ ሀገር በማዘዋወር የምስክርነት ቃል እንዲሰጥ ለማድረግ የሚቀርብ የትብብር ጥያቄ አስመልክቶ እንዴት እንደሚከናወን በአንቀፅ 13 ስር ተደንግጓል፡፡ ግለሰቡ በፈቃዱ ከተዘዋወረ በኋላ ምስክርነቱን ሰጥቶ እስከሚመለከስ በእስር እንደሚቆይ ተገልጸዋል፡፡ ነገር ግን በትብብር ጠያቂ ሀገር ዉስጥ ባለበት ጊዜ እንዲለቀቅ ትብብር አድራጊ ሀገር ካዘዘ ሊለቀቅ እንደሚገባ እና በእስር በትብብር ጠያቂ ሀገር የቆየበት ጊዜም እንደሚታሰብለት ተደንግጓል፡፡ በተጨማሪም በሌላ ሶስተኛ ሀገር በእስር ላይ የሚገን ሰዉ በተመሳሳይ በአንዱ አባል ሀገር በኩል ወደ ሌላዉ አባል ሀገር የሚልያፍበት አጋጣሚ ሲፈጠር( transit) የይለፍ ፈቃድ ሊፈቅዱ እንደሚችሉ ተደንግጓል፡፡
አንቀጽ 14 በምስክርነት፣በባለሙያነት ወይም በግል አቤቱታ አቅራቢነት ግለሰቦች በቪዲዮ ኮንፈረንስ እንዲሰሙ ሲወሰን በትብብር አድራጊ ሀገር ህግ መሰረት በሚመለከተዉ አስፈፃሚ አካል ቁጥጥር ስር ሊደረግ እንደሚገባ ተደንግጓል፡፡
የሚቀርቡት የትብብር ጥያቄዎች ውድቅ ሊሆኑ ስለሚችሉባቸው ምክንያቶች በስምምነቱ አንቀፅ
15 ስር የተገለፀ ሲሆን ምክንያቶቹም፡-
• የቀረበው ጥያቄ ማስተናገዱና ትብብር ማድረጉ የተጠያቂው ሀገር ደህንነት፣ ሉአላዊነት እና መንግስታዊ ስርዓት ላይ ጉዳት የሚያደርስ መሆኑ ሲረጋገጥ፣
• ትብብሩን ማድረግ ጥያቄዉ የቀረበለትን ሀገር ህግ የሚጥስ ከሆነ
• የትብብር ጥያቄው የቀረበው በወታደራዊ ፍርድ ቤት ብቻ የሚያስቀጣ ወይም የፖለቲካ ባህርይ ባለው የወንጀል ጉዳይ መሰረት ተደርጎ ከሆነ
• የትብብር ጥያቄው የቀረበበትን ግለሰብ ማንነቱን፣ ቋንቋን፣ ዜግነትን፣ የፖለቲካ አስተሳሰብን መሰረት በማድርግ ክስ ለማቅረብ ወይም ምርመራ ለማድረግ ከሆነ እና በግለሰቡ ላይ ሰብዓዊ ክብሩን የሚያዋርድ፣ የማሰቃየት እና ኢ- ሰብዓዊ አያያዝ ሊደርስበት ይችላል ተብሎ ሚታሰብ ከሆነ
ናቸዉ፡፡ በነዚህ ምክንያቶች ዉድቅ ከተደረገ ለትብበር ጠያቂ ሀገር ማሳወቅ እንዳለበትም ተደንግጓል፡፡
በአንቀጽ 16 መሰረት የትብብር ጥያቄውን መሰረት በማድረግ ለሚከናወኑ ስራዎች የሚያስፈልገው ወጪ የሚሸፈነው በትብብር ሰጪ ሀገር እንደሚሆን ተደንግጓል፡፡ ነገር ግን ከመደበኛ ወጭዎች የተለየ ከፍ ያለ ወጭ የሚጠይቅ ሲሆን ወጪዎች በጥያቄ አቅራቢ ሀገር በኩል የሚሸፈን ይሆናሉ፡፡
አንቀጽ 17 ቋንቋን የሚመለከት ሲሆን ጥያቄዉ እና ተያያዝ ሰነዶች የሚቀርቡት በትብብር ተጠያቂ ሀገር የስራ ቋንቋ ወይም በአንግሊዝኛ ቅጅ መቅረብ እንዳለበት ይደነግጋል፡፡
አንቀጽ 18 ስምምነቱ ሁለቱም ሀገራት በሌላ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የሚያገኙትን ማንኛዉንም መብት ሆነ የተጣለባቸዉን ግዴታ ሊያስቀር የማይችል መሆኑን ሲደነግግ በአንቀጽ 19 ደግሞ በስምምነቱ አፈፃፀምም ሆነ አተረጓጎም ላይ በሁለቱም ሀገራት ማዕከላዊ ባለስልጣናት የሚነሱ አለመግባባቶች በዲፕሎማሲያዊ መስመር በሚደረግ ምክክር እንደሚፈቱ ተደንግጓል፡፡
በስምምነቱ አንቀጽ 20 ተዋዋይ ሀገራት ይህ ስምምነት ተፈፃሚ በሚሆንበት ጊዜ አንዳቸዉ ከሌላቸዉ የሚያገኙትን ማንኛዉንም መረጃ እና ማስረጃ ስምምነቱ ተግባራዊ በሚሆንበት ጊዜም ሆነ ቀሪ ከሆነ በኋላ ያለሌላኛዉ ሀገር ፈቃድ ለሶስተኛ ሀገር ያለመግለፅ እና ጥበቃ ለማድረግ ተስማምተዋል፡፡
የስምምነቱ አንቀጽ 21 የመጨረሻ ድንጋጌዎችን የያዘ ሲሆን ስምምነቱ ወደ ሥራ የሚገባው በሁለቱም ሀገራት መጽደቁን በሚመለከት ሰነድ በዲፕሎማቲክ መስመር ልውውጥ በተደረገበት ቀን እንደሆነ ተደንግጓል። በተጨማሪም ሀገራቱ የ180 ቀናት የጽሑፍ ቅድመ-ማስታወቂያ በመስጠት የስምምነቱን ተፈጻሚነት ቀሪ ማድረግ እንደሚችሉ ተደንግጓል። ይህም በሚሆንበት ጊዜ ቀድሞ የተጀመሩ የትብብር ሂደቶች ላይ የሚያስከትለዉ ተጽዕኖ የሌለ መሆኑ ተደንግጓል፡፡
6. ማጠቃለያ
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት እና በተርክየ ሪፐብሊክ መንግስት መካከል በወንጀል ጉዳዮች የጋራ የህግ ትብብርን አስመልክቶ የተደረገው ስምምነት ቱርክ እና ኢትዮጵያ ያላቸዉ ግንኙነት ለረጅም ጊዜ የነበረ እና በተለይም ደግሞ በአሁኑ ሰዓትም ዘርፈ ብዙ እና ከዕለት ወደ ዕለት እያደገ በመምጣቱ በተለይም በንግድ እና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ያላቸዉ ግንኙነት እየጨመረ የመጣ በመሆኑ እና በዚህም ምክንያት ኢትጵያውያን በቀላሉ ወደ ቱርክ መጓዝ መቻላቸው የወንጀል ክስ፣ ምርመራ እና ክስ ሂደት የሚስፈልጉ መረጃ እና ማስረጃዎች እንዲሁም ለወንጀል መፈፀሚያነት የዋሉ፣ ሊዉሉ የታሰቡ ወይም የወንጀል ፍሬ የሆኑ ንብረቶች ሊሸሹ የሚችሉበት ዕድል ከፍተኛ ነዉ፡፡ በመሆኑም እነዚህን ጉዳዮች በተመለከተ ለሚደረጉ ትብብሮች በሕግ ማዕቀፍ ምላሽ ለማስጠት ስምምነቱ አስፈላጊ ነዉ። ከዚህ አንጻር በሚኒስትሮች ምክር ቤት እና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውይይት ተደርጎበት እንዲጸድቅ ረቂቅ አዋጁን አያይዘን አቅርበናል።