Contract
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት እና በተባበሩት የአረብ ኤምሬቶች መንግስት መካከል የተደረገውን በወንጀል ጉዳዮች የጋራ የሕግ ትብብር ስምምነት ለማፀደቅ የተዘጋጀ ማብራሪያ
1. መግቢያ
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት እና በተባበሩት የአረብ ኤምሬቶች መንግስት እ.ኤ.አ. ሴፕቴምበር 21 ቀን 2022 በወንጀል ጉዳዮች የጋራ የህግ ትብብር ስምምነት በአቡዳቢ ተፈርሟል።
በስምምነቱ መግቢያ ላይ ስምምነቱ በወንጀል ምርመራ፣ ክስ እና የክርክር ሂደት የሁለቱንም ሀገራት የህግ አካላት ዉጤታማ በማድረግ የወንጀል መከላከል ስራን ዉጤታማነት ለማሳደግ ታስቦ የተፈረመ ስምምነት መሆኑን ይገልፃል፡፡
ስለሆነም ስምምነቱ በወንጀል ጉዳይ የሚደረግ ምርመራን እና ክስ ሂደትን በሚመለከት ለሚደረገው የሁለትዮሽ ትብብር የሕግ ማዕቀፍን የሚፈጥር በመሆኑ በሚኒስትሮች ምክር ቤት እና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውይይት ተደርጎበት እንዲጸድቅ ለማስቻል ይህ መግለጫ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡
2. ስምምነቱ በአገራችን ላይ የሚጥለዉ ግዴታ
ስምምነቱ በወንጀል ጉዳዮች የጋራ የህግ ትብብር ስምምነት እንደመሆኑ በአገራችን ላይ የሚጥላቸው ልዩ ልዩ ግዴታዎች አሉ። ከእነዚህ መካከልም ዋነኛው በተባበሩት የአረብ ኤምሬቶች መንግስት በሚቀርብ የትብብር ጥያቄ መሠረት ስምምነቱን እና ሀገራችን ህግን መሰረት በማድረግ በወንጀል ምርመራ፣ ክስ እና የክርክር ሂደት ላይ ባሉ ጉዳዮች ሚፈለጉ ማስረጃዎችን እና መረጃዎችን የመስጠት እንዲሁም ለወንጀል መፈፀሚያነት የዋሉ፣ ሊዉሉ የታሰቡ ወይም የወንጀል ፍሬ የሆኑ ንብረቶችን የመያዝ፣ የማገድ እና የመዉረስ ግዴታ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ ትብብሩን ለማድረግ የሚወጣው ወጪ በአገራችን በኩል እንዲሸፈን ግዴታን ይጥላል። ነገር ግን ትብብሩን ለማድረግ የሚያስፈልገዉ ወጭ መደበኛ ከሆነዉ ወጭ የተለየ እና ትብብር አድራጊ ሀገርን ከፍተኛ ወጭ የሚያስወጣ ከሆነ ወጭዉን ሁለቱ ሀገራት ትብብሩ የሚፈጸምበት አግባብ በመነጋገር እንደሚወስኑ ተደንግጓል፡፡
ሆኖም በአጠቃላይ የትብብር ስምምነቱ ተፈጻሚነት በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ በሀገራችን በኩል ለተባበሩት የአረብ ኤምሬቶች መንግስት የሚቀርብ ጥያቄ የሚስተናገደው በተባበሩት የአረብ ኤምሬቶች መንግስት የሚቀርብን ጥያቄ ሀገራችን በምታስተናግድበት አግባብ ይሆናል።
3. የስምምነቱ መጽደቅ ለአገራችን የሚኖረዉ ጠቀሜታ
ሀገራችን እየተገበረች ያለችዉን የልማት እና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አጠናክሮ ለማስቀጠል ጉልህ ሚና ከሚጫወቱ ነገሮች መካከል የሕግ የበላይነት መከበር ነው፡፡ የዚህም አንዱ መገለጫ የተለያዩ የወንጀል መረጃዎች/ማስረጃዎች በመለዋወጥ ወንጀለኞች ከቅጣት የማያመልጡበትን ሁኔታ መፍጠር ሲሆን ይህንንም ለማከናወን በእንካ ለእንካ (Principle of Reciprocity) ከሚካሄዱ ትብብሮች ባለፈ በሀገራት መካከል ስምምነቶችን መፈራረም እና ፀድቀው ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረግ ዋናው መሳሪያ ነው፡፡
የተባበሩት የአረብ ኤምሬቶች እና ኢትዮጵያ ያላቸዉ ግንኙነት ለረጅም ጊዜ የነበረ እና በተለይም ደግሞ በአሁኑ ሰዓት ዘርፈ ብዙ እና ከዕለት ወደ ዕለት እያደገ መምጣቱ ይታወቃል፡፡ በተለይም በንግድ እና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ያላቸዉ ግንኙነት እየጨመረ የመጣ በመሆኑ እና በዚህም ምክንያት ኢትጵያውያን በቀላሉ ወደ ተባበሩት የአረብ ኤምሬቶች መጓዝ ለወንጀል ክስ፣ ምርመራ እና ክስ ሂደት የሚያስፈልጉ መረጃ እና ማስረጃዎች እንዲሁም ለወንጀል መፈፀሚያነት የዋሉ፣ ሊዉሉ የታሰቡ ወይም የወንጀል ፍሬ የሆኑ ንብረቶች ሊሸሹ የሚችሉበት ዕድል ከፍተኛ ነዉ፡፡ በመሆኑም እነዚህን ጉዳዮች በተመለከተ ለሚደረጉ ትብብሮች በሕግ ማዕቀፍ ምላሽ ለማሰጠት ስምምነቱ አስፈላጊ ነዉ፡፡
4. የስምምነቱ አፈጻጸም
የስምምነቱን አፈጻጸም በሚመለከት የተቀመጡትን ድንጋጌዎች ለማስፈጸምና ተፈጻሚነታቸውን ለመከታተል ኃላፊነቱን የሚወስድ መንግስታዊ አካል መሰየም አስፈላጊ መሆኑ ይታወቃል። ከዚህ አንፃር የስምምነቱ ይዘት በወንጀል ጉዳዮች የሚደረግ የጋራ ህግ ትብብርን የሚመለከት በመሆኑ የወንጀል ጉዳዮች ትብብር አካል ነዉ ። በዚህ ረገድ የፌዴራል አስፈፃሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣዉ አዋጅ ቁጥር 1263 አንቀጽ 40(1) እና የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግን ለማቋቋም የወጣው አዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀጽ 6 (12) ) መሠረት
የኢፌዴሪ ፍትሕ ሚኒስቴር በወንጀልና በፍትሐብሔር ጉዳዮች ዓለም አቀፍ ግንኙነትና ትብብር እንዲያደርግ ኃላፊነት የተጣለበት በመሆኑ እንዲሁም በስምምነቱ አንቀጽ 7 መሠረት የስምምነቱን አተገባበር ለመከታተል የፍትሕ ሚኒስቴር እንደ ማዕከላዊ ባለስልጣን የተሰየመ በመሆኑ ይህንን ስምምነት ለማስፈጸምና ተፈፃሚነቱን ለመከታተል ኃላፊነት ይኖረዋል፡፡
የስምምነቱ ይዘት
ስምምነቱ በይዘት የትብብር ስምምነቱ ዓላማ፣የተፈፃሚነት ወሰን፣ ጥያቄዉ ማዕከላዊ ባለስልጣናት፣ የጋራ የህግ ትብብሩ ወሰን፣ የትብብር ጥያቄዉ ፎረም እና ይዘት፣ የትብብሩ አፈጻፀም፣ ጊዜያዊ እርምጃዎች፣ የትብብር ጥያቄዉ ውድቅ ሊደረግ ስለሚችልባቸዉ ሁኔታዎች፣ የተለያዩ የትብብር ዓይነቶች ስለሚስተናገዱባቸዉ ሥነ-ሥርዓት እንዲሁም ሌሎች ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችን የያዙ ሃያ ስምንት (28) አንቀጾች አሉት።
በስምምነቱ አንቀጽ 1 የሰምምነቱ ዓላማ በወንጀል ጉዳዮች የጋራ ህግ ትብብር ዙሪያ የትብብር ማዕቀፍ መፍጠር ሲሆን በአንቀጽ 2 መሰረትም ሀገራቱ ሰፊ ሆነ ወንጀል ህግ ትብብር ለማድረግ መስማማታቸዉ ተደንግገጓል፡፡
በአንቀጽ 3 መሰረት ሁለቱ ሀገራት በወንጀል ጉዳች የጋራ የፍትህ ትብብር ለማድረግ ግዴታ የገቡ ሲሆን የጋራ ትብብሩ ወሰንም
• ተጠርጣሪን ቃል መቀበል፣ ምስክር ቃል መቀበል፤
• የፋይንንስ መረጃ እና ወንጀል ሪከርድን ጨምሮ ለምርመራ የሚያግዙ መረጃዎችንና ሰነዶችን መለዋወጥ፣
• በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን እና ዕቃዎችን ማፈላለግ እና መለየት፤
• መጥሪያ ማድረስን፣
• ሰዎችን ለምስክርነት እና ምርመራን እንዲያግዙ መጥራት
• በእስር ላይ የሚገኝ ግለሰብን ለምስክርት ሲፈለግ ወይም ምርመራን እንዲያግዝ ማስተላለፍ፤
• የብርበራ እና የንብረት ማገድ ትዕዛዞችን ማስፈፀም፤
• የወንጀል ፍሬዎችን ማፈላለግ፣ መያዝ እና መዉረስ
• የገንዘብ ቅጣቶችን፣ የካሳ ትዕዛዞችን ማስፈፀም፤
እና ሌሎች ተመሳሳይ የሆኑ ትብበሮችን የሚያካትት ሲሆን ስምምነቱ ወደስራ ከመግባቱ በፊት ለተፈጸሙ ወንጀሎችም ተፈጻሚነት አለዉ፡፡
በአንቀጽ 4 መሰረትም ስለ ሀገራቱ ህግ እና የፍትህ አሰራር በአጠቃላይ መረጃዎችን ሊለዋወጡ እንደሚችሉ ተደንግጓል፡፡
አንቀጽ 5 ስምምነቱ ተፈፃሚ ስለማይሆንባቸዉ ጉዳች ሚደነግግ ሲሆን ለአሳልፎ መስጠት የሚፈለግን ሰዉ ለማሰር፣ የተጠያቂ ሀገር ህግ ከሚፈቅደዉ ዉጭ ለሆነ በጠያቂ ሀገር የተወሰኑ ፍርዶችን ለማስፈፀም፣ እስረኛን ለማስተላለፍ እና ጅምር የወንጀል መዛግብትን ለማስተላለፍ ጉዳች ተፈፃሚነት የለዉም፡፡
አንቀጽ 6 ስምምነቱ ሀገራቱ በሌላ ስምምነቶች መሰረት ያለባቸዉን ትብር የማድረግ ግዴታ የማይገድብ ስለመሆኑ ተደንግጓል፡፡
በስምምነቱ አንቀጽ 7 በሀገራችን በኩል የፍትሕ ሚኒስቴር እንዲሁም በተባበሩት የአረብ ኤምሬቶች በኩልም የፍትሕ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ማዕከላዊ ባለስልጣን (central Authorities) እንዲሆኑ ተሰይመዋል፡፡ ግንኑታቸዉም በዲፕሎማቲክ ቻናሉ በኩል መሆን እንዳለበት እና አስቸኳይ ሁኔታ ሲያጋጥም በቀጥታ መገናኘት እንደሚችሉ ተደንግጓል፡፡
አንቀጽ 8 ስለ ትብብር ጥቄዉ ፎርም እና ይዘት ሚደነግግ ሲሆን የትብብር ጥያቄ በፅሑፍ ሊቀርብ እንደሚገባ፤ ነገር ግን አስቸኳይ ሁኔታ ሲያጋጥም በኤሌክትሮኒክ መንገድ ሊላክ እንደሚችልና በ 30 (ሰላሳ) ቀን ዉስጥ በፅሁፍ በዲፕሎማቲክ ቻናሉ በኩል ሊላክ እንደሚገባ ተደንግጓል፡፡
በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (2) መሰረት የተኛዉም የትብብር ጥያቄ የሚከተሉትን መያዝ አለበት፡-
• ምርመራዉን እያደረገ ያለዉ ወይም የወንጀል ሂደቱን እየተከታተለ ያለዉ አካል ስም
• የትብብሩ ዓላማ እና ተፈለገዉን ትብብር ምንነት
• የወንጀሉን ዓይነት እና ያለበትን ደረጃ ፣ የፍሬ ነገር እና የህግ አጭር መግለጫ ወንጀሉ ሊያስቀጣ የሚችለዉ ከፍተኛ ቅጣት ማብራሪ
• የተፈለገዉን ማስረጃ፣ መረጃ ወይም ሌላ ትብብር መግለጫ
• ትብብር አድራጊ ሀገር ሊከተል የሚገባዉ የተለየ ስነስርዓት ስለመኖሩ እና ምክንያቱን
• ትብብሩ ሊፈፀም የሚገባበት ጊዜ ገደብ
• የሚስጥራዊነት አስፈላጊነት እና ምክንያቱ
• በተጠያቂ ሀገር ዉስጥ የሚያስፈልጉ ሌሎች መረጃዎችን እና ስነስርዓቶችን በተጨማሪም በንዑስ አንቀጽ (3) መሰረት የሚከተሉትነ ሊይዝ ይችላል፡-
• ምርመራዉ ወይም የወንጀል ሂደቱ እየተፈፀመበት ያለዉን ሰዉ ማንነት፣ ዜግነት እና የሚገኝበትን ቦታ፤
• መረጃ አለበት የተባለዉን ሰዉ ማንነት እና የሚገኝበትን ቦታ፤
• ሰነድ ወይም መረጃ የሚደርሰዉ ሰዉ ማንነት እና የሚገኝበትን ቦታ፤ከጉዳ ጋ ያለዉ ግንኙነት እና የአደራረሱ አግባብ ወይም ስነስርዓት፤
• የሚፈለገዉን ሰዉ ማንነት እና የሚገኝበትን ቦታ የሚመለከት መረጃ፤
• የምስክርነት ቃል ወይም ተከሳሽነት ቃል እንዲመዘገብ የሚያስፈልግ የተለየ ስነስርዓት፤
• ምስክሩ እንዲጠየቅ የሚፈለገዉ ጥያቄ ዝርዝር፤
• ሌሎች ማስረጃዎች እንዲሰበሰቡ የሚያስፈልጉበት አግባብ፣ የቃለ መሐላ አስፈላጊነት እና የጠያቂ አካልን ፊርማ እና ማህተም ናቸዉ፡፡
በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (4) መሰረት ማንኛዉም የትብብር ጥያቄ እና ደጋፊ ሰነድ በትብብር ተጠያቂ ሀገር የስራ ቋንቋ ወይም በአንግሊዝኛ ትርጉም መቅረብ ያለበት መሆኑ ተደንግጓል፡፡
በስምምነቱ አንቀጽ 9 መሰረት ትብብር የተጠየቀ ሀገር ትብብሩን ለመፈፀም የሚያስፈልጉት ተጨማሪ ማስረጃዎች ካስፈለጉት ትብብር የጠየቀዉን ሀገር እንዲያሟላ መጠየቅ እንደሚችል እና ትብብር የጠየቀዉን ሀገርም መረጃዎቹና የመስጠት ግዴታ እንዳለበት ተደንግጓል፡፡ የሚቀርቡት የትብብር ጥያቄዎች ውድቅ ሊሆኑ ስለሚችሉባቸው ምክንያቶች በስምምነቱ አንቀፅ
10 ስር የተገለፀ ሲሆን በንዑስ አንቀጽ 1 አስገዳጅ (mandatory grounds for refusal) በ በንዑስ አንቀጽ 2 ፈቃጅ ምክንያቶች (Discretionary grounds of refusal) ተዘርዝረዋል፡- አስገዳጅ የትብብር ዉድቅ ማድረጊያ ምክንያቶች (mandatory grounds for refusal)
• ጥያቄ የቀረበበት የወንጀል ድርጊት በወታደራዊ ወንጀልነት ብቻ የሚያስቀጣ ከሆነ፤
• የተጠየቀዉን ጉዳይ በተመለከተ የተጠየቀዉ ሀገር በጉዳዩ ላይ በመጨረሻ ፍርድ በነፃ የተሰናበተ፣ ቅጣት የተላለፈበት ወይም ቅጣቱን ፈጽሞ የጨረሰ ከሆነ፤
• ጥያቄው የቀረበለት አገር ጥያቄው የቀረበው ግለሰቡን በዘሩ፣ በኃይማኖቱ፣ በዜግነቱ፣ በጾታው፣ በፖለቲካ አመለካከቱ ወይም በመሰል ምክንያቶች ለመክሰስ መሆኑን በሚመለከት በቂ መረጃ ሲኖረው፤
• ትብብር ማድረግ የትብብር አድራጊ ሀገርን ሉዓላዊነት፣ ደህንነት፣ የማህበረሰብ ስርዓት እና መሰረታዊ ጥቅም ሊጉዳ የሚችል ሲሆን ናቸዉ፡፡
ፈቃጅ ምክንያቶች (Discretionary grounds of refusal) ደግሞ ፡-
• የትብብር ጥያቄው የቀረበው በወታደራዊ ፍርድ ቤት ብቻ የሚያስቀጣ ወይም የፖለቲካ ባህርይ ባለው የወንጀል ጉዳይ መሰረት ተደርጎ ከሆነ ሲሆን በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በኩል በፕሬዝዳንቱ፣በምክትል ፕሬዝዳንቱ፣ በጠቅላይ ሚኒስቴሩ፣ በማንኛዉም የፌዴራል ጠቅላይ ምክር ቤት (Federal Suprem Council) አባል እና በቤተሰቦቻቸዉ ላይ የተሰነዘረ ጥቃት፤ በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ በማንኛዉም ሰዉ ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች እንደ ፖለቲካ ወንጀሎች የማይቆጠሩ ሲሆን በተጨማሪም በሌሎች ሀገሮቹ አባል በሆኑባቸዉ የባለ ብዙ ወገን ስምምነቶች መሰረት እንደ ፖለቲካ ወንጀል የማይቆጠሩ ወንጀሎች፣ የሰዉ መግደል ወንጀል፣ ሽብርተኛነት እና በነዚህ ወንጀሎች ማሴር፣ ሙከራ ማድረግ እና ወንጀለኛን በመርዳት መሳተፍ ወንጀሎች እንደ ፖለቲካ ወንጀሎች አይቆጠሩም፡፡
• ድርጊቱ በተጠያቂ ሀገር እንደወንጀል የማይቆጠር ከሆነ፤
• የተጠየቀዉን ጉዳይ በተመለከተ የተጠየቀዉ ሀገር በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ ፍርድ የተላለፈበት ከሆነ፤
• ትብሩን ማድረግ ከተጠያቂ ሀገር ህግ ጋር ሚቃረን ከሆነ ናቸዉ፡፡
ነገር ግን የባንክ ምስጢራዊነትን መሰረት በማድረግ ብቻ መቃወም እንደማቻል እንደሁም ትብሩን ከመቃወም በፊት በተወሰነ ቅድመ ሁኔታ ትብብር ማድረግ የሚቻልበት አግባብ ካለ እንዲታ እና ትብብሩ ዉድቅ ከተደረገ በፍጥነት ለጠያቂ ሀገር ማሳወቅ እንደሚገባ ተደንግጓል፡፡ አንድ የቀረበ የትብብር ጥያቄ ከትብበር ተጠያቂ ሀገር የውስጥ ህጎች ጋር እስካልተቃረነ ድረስ በሚመለከተው የመንግስት ተቋም ተግባራዊ ሊደረግ እንደሚገባው እንዲሁም ይህን አስመልክቶ ለጥያቄ አቅራቢ ሀገር ማሳወቅ እንደሚገባ በስምምቱ አንቀፅ 11 ስር ተደንግጓል፡፡
አንቀጽ 12 በትብብሩ አማካኝነት የተለዋወጧቸዉ ሰነዶች እና ንብረቶች የተላለፉበትን ዓላማ ካጠናቀቁ ወደ መጡበት ሀገር ሊመለሱ እንደሚገባ ይደነግጋል፡፡
አንቀጽ 13 ስለ ምስጢራዊነት እና ስለ ዉስን የመረጃ አጠቃቀም የሚደነግግ ሲሆን ትብብር የተጠየቀ ሀገር ማንኛዉንም የትብብር ጥያቄ፣ ከጥያቄዉ ጋር ተያይዘዉ የሚቀርቡ ሰነዶች እና ትብብሩን ለማድረግ የተወሰዱ እርምጃዎች ምስጢራዊ መሆን አለባቸዉ፡፡ ነገር ግን ምስጢራዊነትን ጠብቆ ትብበሩን ለመፈፀም የማይቻል ከሆነ ለትብብር ጠያቂ ሀገር ማሳወቅ እና ፈቃድ ማግኘት ያስፈልጋል፡፡ ትብብር የተጠየቀ ሀገር በትብብሩ መሰረት የሚገኝ ማንኛዉንም መረጃ እና ማስረጃ ለተፈለገበት የወንጀል ምርመራ እና የክስ ሂደት ብቻ የመጠቀም እና መረጃዎቹን ከመጥፋት፣ካልተፈቀደ ተደራሽነት፣ ከመቀየር እና አላግባብ ጥቅም ላይ እንደቻዉል ጥበቃ የማድረግ ኃላፊነት ያለበት ሲሆን መረጃዎቹን እና ማስረጃዎቹን ከተጠየቀበት የትብብር ጉዳይ ዉጭ ያለ ትብብር አድራጊ ሀገር ቅድመ ፈቃድ ያለመጠቀም (restricted use) ግዴታ አለበት፡፡
የስምምነቱ አንቀጽ 14 ሰነዶችን ለማድረስ የሚደረግን ትብብር የሚመለከት ሲሆን የትብብር ጠያቂ ሀገር የዉስጥ ህግ በሚፈቅደዉ መሰረት ትብብር የማድረስ ግዴታ ያለበት ሲሆን ትብብር ተጠያቂ ሀገር ሰነዱን ለሚመለከተው ሰው ምክንያታዊ በሆነ ጊዜ በማድረስ ሰነዱን ያስረከበ ስለመሆኑ የሚያሳይ ማረጋገጫ ለትብብር አቅራቢ ሀገር መስጠት ይኖርበታል፡፡ ሰነዶቹን ማድረስ ካልቻለም ምክንያቱን በመግለጽ ማሳወቅ አለበት፡፡ ነገር ግን መጥሪያ የደረሰዉ ሰዉ በተጠየቀዉ መሰረት ካልቀረበ በትብብር አድራጊም ይሁን ጠያቂ ሀገር ምንም ዓይነት ቅጣት ወይም የማስገደድ እርምጃ አይደርስበትም፡፡
ስምምነቱ አንቀጽ 15 በትብብር ተጠያቂ ሀገር ከሚገኝ ግለሰብ ቃል ለመቀበል ወይም ማስረጃ ለማግኘት ስለሚጠየቅ ትብብር የሚደነግግ ሲሆን በዚህ ድንጋጌ መሰረት ለተተቀሰዉ ዓላማ ትብብር የተጠየቀ ሀገር የዉስጥ ህግ እስከሚፈቅደዉ ድረስ ትብብር የማድረግ ግዴታ አለበት፡፡ የትብብሩ ዓይነት በቀጥታ ምስክሩን አግኝቶ ቃል መቀበልን፣ የምስክርነት ቃል ተቀብሎ እንዲላክ መጠየቅን እና ማንኛዉንም ለማስረጃነት የሚያገለግል ሰነድ ወይም ቁስ እንዲመጣ ማድረግን ያጠቃልላል፡፡ በተጠያቂ ሀገር የሚገኝ ትብብሩ የሚመለከተዉ ሰዉ ወይም ህጋዊ ወኪሉ በጠያቂ ወይም በተጠያቂ ሀገር ህግ መሰረት ማስረጃ መስጠቱን መቃወም ይችላል፡፡ በትብብር አድራጊ ሀገር ውስጥ በእስር የሚገኝ ፍርደኛ ግለሰብ በጊዜያዊነት ወደ ትብብር ጠያቂ ሀገር በማዘዋወር የምስክርነት ቃል እንዲሰጥ ለማድረግ የሚቀርብ የትብብር ጥያቄ አስመልክቶ
እንዴት እንደሚከናወን በአንቀፅ 16 ስር ተደንግጓል፡፡ ግለሰቡ በፈቃዱ ከተዘዋወረ በኋላ ምስክርነቱን ሰጥቶ እስከሚመለከስ ትብበር አድራጊ ሀገር ከጠየቀ በእስር እንደሚቆይ ነገር ግን በትብብር ጠያቂ ሀገር ዉስጥ ባለበት ጊዜ እንዲለቀቅ ትብብር አድራጊ ሀገር ካዘዘ ሊለቀቅ እንደሚገባ እና በእስር በትብብር ጠያቂ ሀገር የቆየበት ጊዜም እንደሚታሰብለት ተደንግጓል፡፡ የስምምነቱ አንቀጽ 17 ማስረጃ ወይም ሌላ ድጋፍ እንዲሰጥ ስለሚፈለግ ሰዉ የሚመለከት ሲሆን በዚህ ዙሪያ ጥሪዉን ለተፈላጊዉ ሰዉ እንዲደርስ ትብብር የተጠየቀ ሀገር ትብብር ማድረግ እንዳለበት እና ትብብር የጠየቀ ሀገርም ስለ ሰዉየዉ ደህንንት አስፈላጊዉን እንደሚያሟላ ይደነግጋል፡፡ ግለሰቡ ፈቃደና ከሆነ ትብብር የተጠየቀዉ ሀገር ግለሰቡ ትብብሩን እንዲያደርግ የሚያስችሉ አስፈላጊ እገዛወችን ማድረግ እንዳለበት ነገር ግን ግለሰቡ ፈቃደኛ ካልሆነ ምንም ዓይነት ቅጣት ወይም የማስገደድ እርምጃ እንደማይወሰድበት ተደንግጓል፡፡ የስምምነቱ አንቀጽ 18 ሁለቱ ሀገራት ለፍትህ አስፈላጊ ሆነ ሲገኝ እና ለፍጥነት ሲባል የቪዲዮ ኮንፈረንስ እና ሌሎች የምስል ወድምጽ መገናኛ ዘዴዎችን ለመጠቀም በማንኛዉም ጊዜ ሊስማሙ እንደሚችሉ ተደንግጓል፡፡
የስምምነቱ አንቀጽ 19 በሌላ ሶስተኛ ሀገር በእስር ላይ የሚገኝ ሰዉ ለህግ ጉዳዮች የጋራ ፍትሕ ትብብር ዓላማ በአንዱ አባል ሀገር በኩል ወደ ሌላዉ አባል ሀገር የሚልያፍበት አጋጣሚ ሲፈጠር (transit) የይለፍ ፈቃድ ሊፈቅዱ እንደሚችሉ እና እስከሚተላለፍ ድረስ በእስር ላይ ለማቆየት ካስፈለገ ሊስማሙ እንደሚችሉ ተደንግጓል፡፡
የስምምነቱ በአንቀጽ 20 በእስር ላይ የሚገኝ ሰዉ ለህግ የጋራ ትብብር ዓላማ በትብብር ጠያቂ ሀገር ከተላለፈ በኋላ ቀድሞ በሰራዉ ሌላ የወንጀል ጉዳይ ምክንያት ሊያዝ፣ ሊከሰስ ወይም ሊታሰር እንደማይችል እንዲሁም በዛ ሀገር ባይገኝ ኖሩ ሊጠየቅ በማይችልበት የፍትሐብሔር ጉዳይ ሊጠየቅ እንደማይችል ተደንግጓል። በተጨማሪም ከተላለፈበት ጉዳይ ዉጭ ያለ ፈቃዱ መረጃ እንዲሰጥ ወይም ትብብር እንዲያደርግ እንደማይገደድ ተደንግጓል፡፡ ሆኖም ግለሰቡ ከጠያቂ አገር ወጥቶ በፈቃደኝነት ወደዛው ሀገር ከተመለሰ፣ ግለሰቡ ነፃ ከተደረገ በኋላ ከሀገሪቱ መዉጣት እየቻለ በ 30 ቀናት ውስጥ ከጠያቂ አገር ካልወጣ ግን ሊያዝ፣ ሊከሰስ ወይም ሊታሰር እንደሚችል ተገልጧል፡፡
የስምምነቱ አንቀጽ 21 በተጠያቂ ሀገር የሚገኙ ለሁሉም ክፍት የሆኑ (Publicly available) ሰነዶችን እና በመንግስት መስሪያ ቤቶች የሚገኙ ሰነዶችን (Official Documents) የሚመለከት
ሲሆን ለሁሉም ክፍት የሆኑ (publicly available) ሰነዶችን ለማቅረብ ግዴታ ያለበት ሲሆን በመንግስት መስሪያ ቤቶች የሚገኙ ሰነዶችን ኮፒ ደግሞ ሊተባበሩ እንደሚችሉ ተደንግጓል፡፡ የስምምነቱ አንቀጽ 22 ስለ ብርበራ እና መያዝን ስለሚመለከት ትብብር የሚመለከት ሲሆን በዚህ ረገድ ለሚጠየቅ ትብብር የሀገራቸዉ ህግ እስከሚፈቅደዉ ድረስ ትብብር ማድረግ እንደሚገባቸዉ ትብብር የሚጠይቅ ሀገርም አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን መስጠት ያለበት መሆኑን፣ ትብበር የሚያደርግ ሀገርም ስለተበረበረዉ ንብረት፣ ስለተያዘዉ ዕቃ እና አጠቃላይ ሁኔታዎች መረጃ የመስጠት ግዴታ ያለበት መሆኑን እንዲሁም ትብብር የጠየቀ ሀገር የተያዘዉን እቃ በተመለከተ ትብብር የሚያደርገዉ ሀገር የሚያስቀምጠዉን ቅድመ-ሁኔታ ማክበር ግዴታ እንዳለበት ተደንግጓል፡፡
የስምምነቱ አንቀጽ 23 ከትብብር ጠያቂ ሀገር የህዝብና መንግስት ሀብት የተመዘበረ (በህገወጥ መንገድ ተገኝቶ እና ህጋዊ መስሎ የቀረበም ይሁን አይሁን) ትብብር በተጠየቀ ሀገር የተገኘ የተያዘና የተወረሰ ንብረት ንብረቱን ለመያዝ እና ለመዉረስ የወጣ ወጭ ብቻ ተቀንሶ የቀረዉ ንብረት ወደ ትብብር ጠያቂ ሀገር የመመለስ ግዴታ ትብብር በተጠየቀ ሀገር ላይ ይጥላል፡፡ ንብረት የመመለስ ተግባርም የሚፈፀመዉ በትብብር ጠያቂ ሀገር የሚደረግን መጨረሻ ዉሳኔ መሰረት በማድረግ ነዉ፡፡
የስምምነቱ አንቀጽ 24 በወንጀል የተገኘ ገንዘብ ወይም የወንጀል መፈፀሚያነት ያገለገለ ንብረት በትብብር ተጠያቂ የሚገኝ ከሆነ ገንዘቡን ለማፈላለግ ጥረት ማድረግ ግዴታ ያለበት ሲሆን ትብብር የጠየቀ ሀገርም ገንዘቡ ወይም ንብረቱ በትብብር ተጠያቂ ሀገር የሚገኝ ስመሆኑ ለመጠርጠር የቻለበትን ምክንያት መግለጽ ይኖርበታል፡፡ እነዚህ ንብረቶች በሚገኙ ጊዜ የመጨረሻ ፍርድ በትብብር ጠያቂ ሀገር እስኪሰጥ ድረስ ትብብር የተጠየቀ የዉስጥ ህጉ እስከሚፈቅደዉ ድረስ የትብብር ጠያቂ ሀገር ንብረቶቹ ወደሶስተኛ ወገን እንዳተላለፉ እና አንዳይባክኑ የሚያስፈልገዉን እርምጃ መዉሰድ አለበት፡፡ ትብብር የተጠየቀ ሀገር የቅንልቦና ሶስተኛ ወገኖችን ጥቅም እንደማይጎዳ በማረጋገጥ የዉስጥ ህጉ በሚፈቅደዉ ልክ ለትብብር ጠያቂ ሀገር መመለስ ግዴታ አለበት፡፡
የስምምነቱ አንቀጽ 25 የሰነዶችን ተቀባይነት የሚመለከት ሲሆን ሁለቱ ሀገራት የሚለዋወጧቸዉ ማንኛዉም ሰነዶች መረጋገጥ (Authentication) የማያስፈልጋቸዉ መሆኑ ተደንግጓል፡፡ ነገር ግን ከሁለቱ ሀገራት አንዳቸዉ በሚጠይቁበት ጊዜ ሰነዶች የማረጋገጥ ግዴታ አለባቸዉ፡፡
የስምምነቱ አንቀጽ 26 ትብብር የጠየቀ ሀገርን በትብብር ተጠያቂ ሀገር በሚደረጉ ሂደቶች ዉክልና እና ወጭን የሚመለከት ነዉ፡፡ በዘህ አንቀጽ መሰረት ትብብር ተጠያቂ ሀገር የዉስጥ ህጉ በሚፈቀድለት ልክ ትብብር የጠየቀ ሀገር በሂደቶቹ እንዲወከል የማድረግ ወይም የመወከል ግዴታ አለበት፡፡ የትብብር ጥያቄውን መሰረት በማድረግ ለሚከናወኑ ስራዎች የሚያስፈልገው ወጪ የሚሸፈነው በትብብር ሰጪ ሀገር እንደሚሆን ተደንግጓል፡፡ ነገር ግን ከመደበኛ ወጭዎች የተለየ ከፍ ያለ ወጭ የሚጠይቅ ሲሆን ወጪዎች በጥያቄ አቅራቢ ሀገር በኩል የሚሸፈን ይሆናሉ፡፡
በስምምነቱ አንቀጽ 27 ደግሞ በስምምነቱ አፈፃፀምም ሆነ አተረጓጎም ላይ በሁለቱም ሀገራት ማዕከላዊ ባለስልጣናት የሚነሱ አለመግባባቶች በዲፕሎማሲያዊ መስመር በሚደረግ ምክክር እንደሚፈቱ ተደንግጓል፡፡
የስምምነቱ አንቀጽ 28 የመጨረሻ ድንጋጌዎችን የያዘ ሲሆን ስምምነቱ ወደ ሥራ የሚገባው በሁለቱም ሀገራት መጽደቁን በሚመለከት ሰነድ በዲፕሎማቲክ መስመር የመጨረሻዉ ልውውጥ ከተደረገበት ከ30 ቀናት በኋላ እንደሆነ ተደንግጓል። ስምምነቱ በሀገራቱ የጋራ ፈቃድ ላይ ተመስርቶ መሻሸል እንደሚችል፤ተፈፃሚነቱ ስምምነቱ ከመፈረሙ በፊት ለተፈፀሙ ወንጀሎችም መሆን እንዳለበት፣ በተጨማሪም ሀገራቱ የ180 ቀናት የጽሑፍ ቅድመ- ማስታወቂያ በመስጠት የስምምነቱን ተፈጻሚነት ቀሪ ማድረግ እንደሚችሉ ተደንግጓል። ይህም ቀድሞ የተጀመሩ ሂደቶች ላይ የሚያስከትለዉ ተጽዕኖ የሌለ መሆኑ ተደንግጓል፡፡ በመጨረሻም ስምምነቱ ወደ ስራ ከገባበት ጊዜ በፊት የተፈፀሙ ወንጀሎችን ጨምሮ በሀገራቱ በሚቀርቡ ማንኛዉም ጥያቄዎች ላይ ተፈፃሚ እንደሚደረጉ ተደንግጓል፡፡
ማጠቃለያ
የተባበሩት የአረብ ኤምሬቶች እና ኢትዮጵያ ያላቸዉ ግንኙነት ለረጅም ጊዜ የነበረ እና በተለይም ደግሞ በአሁኑ ሰዓት ዘርፈ ብዙ እና ከዕለት ወደ ዕለት እያደገ መምጣቱ ይታወቃል፡፡ በተለይም በንግድ እና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ያላቸዉ ግንኙነት እየጨመረ የመጣ
በመሆኑ እና በዚህም ምክንያት ኢትጵያውያን በቀላሉ ወደ ተባበሩት የአረብ ኤምሬቶች መጓዝ ለወንጀል ክስ፣ ምርመራ እና ክስ ሂደት የሚያስፈልጉ መረጃ እና ማስረጃዎች እንዲሁም ለወንጀል መፈፀሚያነት የዋሉ፣ ሊዉሉ የታሰቡ ወይም የወንጀል ፍሬ የሆኑ ንብረቶች ሊሸሹ የሚችሉበት ዕድል ከፍተኛ ነዉ፡፡ በመሆኑም እነዚህን ጉዳዮች በተመለከተ ለሚደረጉ ትብብሮች በሕግ ማዕቀፍ ምላሽ ለማስጠት ስምምነቱ አስፈላጊ ነዉ። ከዚህ አንጻር በሚኒስትሮች ምክር ቤት እና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውይይት ተደርጎበት እንዲጸድቅ ረቂቅ አዋጁን አያይዘን አቅርበናል።