Contract
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት እና በቱርክ ሪፐብሊክ መንግስት መካከል የተደረገውን የአሳልፎ መስጠት ስምምነት ለማፀደቅ የተዘጋጀ ማብራሪያ (መግለጫ)
ጥር 2015 ዓ.ም
1. መግቢያ
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት እና በቱርክ ሪፐብሊክ መንግስት መካከል እ.ኤ.አ. ሜይ 10 ቀን 2022 በወንጀል ጉዳይ የሚፈለጉ ግለሰቦችን አሳልፎ የመስጠት ስምምነት በአንካራ ተፈርሟል። በስምምነቱ መግቢያ ላይ ስምምነቱ ወንጀልን በመከላከል እና የወንጀል ስነ-ስርዓት ሂደትን በተመለከተ ዓለም አቀፍ አሰራርን መሰረት ያደረገ ዉጤታማ የሆነ የወንጀል መከላከል ትብብር ለማድረግ ታስቦ የተፈረመ ስምምነት መሆኑን ይገልፃል፡፡
ስለሆነም ስምምነቱ በወንጀል ጉዳይ የሚፈለጉ ተጠርጣሪ ወይም ፍርደኞችን አሳልፎ በመስጠት ረገድ ለሚደረገው የሁለትዮሽ ትብብር የሕግ ማዕቀፍን የሚፈጥር በመሆኑ በሚኒስትሮች ምክር ቤት እና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውይይት ተደርጎበት እንዲጸድቅ ለማስቻል ይህ መግለጫ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡
2. ስምምነቱ በአገራችን ላይ የሚጥለዉ ግዴታ
ስምምነቱ በወንጀል ጉዳዮች ግለሰቦችን አሳልፎ ለመስጠት የተደረገ ስምምነት እንደመሆኑ በአገራችን ላይ የሚጥላቸው ልዩ ልዩ ግዴታዎች አሉ። ከእነዚህ መካከልም ዋነኛው በቱርክ ሪፐብሊክ መንግስት በሚቀርብ ጥያቄ መሠረት አሳልፎ ለመስጠት በሚያበቃ የወንጀል ድርጊት ምክንያት ለክስ ወይም ቅጣት እንዲፈጸምበት የሚፈለግን በአገራችን የሚገኝ ግለሰብ አሳልፎ የመስጠት ግዴታ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ ተላልፎ የሚሰጠውን ግለሰብ በአገር ውስጥ ለመያዝ የሚወጣው ወጪ እና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ተላልፎ የሚሰጠው ግለሰብ ወንጀሉን ለመፈፀም የተጠቀመበትን ንብረት ለመያዝና ለማስተላለፍ የሚያስፈልገውን ወጪ በአገራችን በኩል እንዲሸፈን ግዴታን ይጥላል። ነገር ግን ተፈላጊዉን ወደ ተርክዬ ለማጓጓዝ የሚያስፈልግ የትራንስፖርት ወጭን አይጨምርም፡፡
በሌላ በኩል በስምምነቱ አንቀጽ 10 መሠረት አስቸኳይ ሁኔታ በሚፈጠርበት ጊዜ አሳልፎ የመስጠት ጥያቄ ከመቅረቡ በፊት በወንጀል የሚፈለገው ግለሰብ በጊዜያዊነት በቁጥጥር ሥር እንዲውል በቱርክ ወገን በሚጠየቅበት ጊዜ የጉዳዩን አግባብነት ተገንዝቦ ተፈጻሚ ማድረግ አስፈላጊ ይሆናል።
ሆኖም በአጠቃላይ የትብብር ስምምነቱ ተፈጻሚነት በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ በአገራችን በኩል በቱርክ መንግስት የሚቀርብ ጥያቄ የሚስተናገደው በቱርክ መንግስት የሚቀርብን ጥያቄ አገራችን በምታስተናግድበት አግባብ ይሆናል።
3. የስምምነቱ መጽደቅ ለአገራችን የሚኖረዉ ጠቀሜታ
ሀገራችን የጀመረችውን የልማት እና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አጠናክሮ ለማስቀጠል ጉልህ ሚና ከሚጫወቱ ነገሮች መካከል የሕግ የበላይነት መከበር ነው፡፡ የዚህም አንዱ መገለጫ ወንጀል ፈፅመው ከሀገር የሚሸሹ ወንጀለኞችን ለፍርድ የማቅረብ ሂደት ሲሆን ይህንንም ለማከናወን በእንካ ለእንካ መርህ መሰረት ከሚካሄዱ ትብብሮች በተጨማሪ በሀገራት መካከል ስምምነቶችን መፈራረም እና ፀድቀው ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረግ ዋናው ነው፡፡
ኢትዮጵያ እና ቱርክ ያላቸዉ ግንኙነት ለረጅም ጊዜ የነበረ እና በተለይም ደግሞ በአሁኑ ሰዓትም ዘርፈ ብዙ እና ከዕለት ወደ ዕለት እያደገ መምጣቱ ይታወቃል፡፡ በተለይም በ ንግድ እና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ያላቸዉ ግንኙነት እየጨመረ የመጣ በመሆኑ እና በዚህም ምክንያት ኢትጵያውያን በቀላሉ ወደ ቱርክ መጓዝ መቻላቸው ወንጀለኞችም ይህንን ሁኔታ በመጠቀም ከሕግ ለማምለጥ ወደ ቱርክ ለመሄድ የሚችሉበት አጋጣሚ መኖሩ ታሳቢ ሲደረግ ይህን ተከትለው የሚመጡ የአሳልፎ መስጠት ትብብር ጉዳዮችን በሕግ ማዕቀፍ ምላሽ ለማስጠት ስምምነቱ አስፈላጊ መሆኑን ያመላክታል፡፡
4. የስምምነቱ አፈጻጸም
የስምምነቱን አፈጻጸም በሚመለከት የተቀመጡትን ድንጋጌዎች ለማስፈጸምና ተፈጻሚነታቸውን ለመከታተል ኃላፊነቱን የሚወስድ መንግስታዊ አካል መሰየም አስፈላጊ መሆኑ ይታወቃል። ከዚህ አንፃር የስምምነቱ ይዘት በወንጀል ጉዳዮች ወንጀለኞችን አሳልፎ መስጠትን የሚመለከት በመሆኑ የወንጀል ጉዳዮች ትብብር አካል ነዉ። በዚህ ረገድ የፌዴራል አስፈፃሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣዉ አዋጅ ቁጥር 1263 አንቀጽ 40(1) እና የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግን ለማቋቋም የወጣው አዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀጽ 6 (12) ) መሠረት የኢፌዴሪ ፍትሕ ሚኒስቴር በወንጀል ና በፍትሐብሔር ጉዳዮች ዓለም አቀፍ ግንኙነትና ትብብር እንዲያደርግ ኃላፊነት የተጣለበት በመሆኑ እንዲሁም በስምምነቱ አንቀጽ 2 መሠረት የስምምነቱን አተገባበር ለመከታተል የፍትሕ ሚኒስቴር እንደ ማዕከላዊ ባለስልጣን የተሰየመ በመሆኑ ይህንን ስምምነት ለማስፈጸምና ተፈፃሚነቱን ለመከታተል የፍትሕ ሚኒስቴር ኃላፊነት ይኖረዋል፡፡
5. የስምምነቱ ይዘት
ስምምነቱ በይዘት ረገድ አሳልፎ ስለመስጠት ግዴታ፣ የትብብር ጥቄዉ ሚላክበት አካል እ የግንኙነት መስመር፣ አሳልፎ ለመስጠት ስለሚያበቁ የወንጀል ድርጊቶች (Extraditable Offences) ፣ አሳልፎ የመስጠት ጥያቄ ውድቅ ሊደረግ ስለሚችልባቸዉ ሁኔታዎች፣ አሳልፎ የመስጠት ጥያቄ ስለሚስተናገድበት ሥነ-ሥርዓት እንዲሁም ሌሎች ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችን የያዙ ሃያ አራት (24) አንቀጾች አሉት።
በስምምነቱ አንቀጽ 1 መሠረት ሀገራቱ በጠያቂ ሀገር አሳልፎ ለመስጠት በሚያበቃ የወንጀል ድርጊት ለክስ ወይም ቅጣት እንዲፈጸምበት የሚፈለግን ግለሰብ አሳልፎ ለመስጠት ግዴታ ገብተዋል።
በስምምነቱ አንቀጽ 2 መሠረት የሚቀርቡ የአሳልፎ መስጠት ጥያቄዎችን ለማስተናገድ እንዲቻል በሀገራቱ መካከል የሚደረገው ግንኙነት በዲፕሎማሲያዊ መስመሩ መሆን እንዳለበት ያስቀመጠ ሲሆን በአገራችን በኩል የፍትሕ ሚኒስቴር በቱርክ በኩልም የፍትሕ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ማዕከላዊ ባለስልጣን (central Authorities) እንዲሆኑ ተሰይመዋል፡፡
ስምምነቱ አንቀጽ 3 መሰረት አሳልፎ ለመስጠት የሚያበቃ የወንጀል ድርጊቶች ማለት አሳልፎ የመስጠት ጥያቄው በቀረበበት ጊዜ በሁለቱም አገራት ሕግ ቢያንስ በአንድ ዓመት ቀላል እስራት ሊያስቀጣ የሚችል የወንጀል ድርጊት መሆኑን አስቀምጧል። ሆኖም አሳልፎ የመስጠት ጥያቄው የቀረበው በፍርድ ቤት የተላለፈ የቅጣት ውሣኔን ለማስፈጸም በሚሆንበት ጊዜ ቀሪው የቅጣት ጊዜ ቢያንስ ስድስት ወር ሊሆን እንደሚገባ ተደንግጓል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የአሳልፎ መስጠት ጥያቄው የሚቀርብለት አካል የወንጀሉን ዓይነት ሲመረምር በጠያቂው ሀገር ሕግ አገላለፅ እና በተጠያቂው ሀገር ህግ አገላለፅ ልዩነት መኖሩ ወይም ወንጀሎቹ የሚመደቡበት ክፍል (category of offences) የተለያየ መሆኑ ልዩነት እንደማይፈጥር ያስቀምጣል፡፡
የስምምነቱ አንቀጽ 4 እና 5 አሳልፎ የመስጠት ጥያቄ ውድቅ ሊደረግ የሚችልባቸውን ሁኔታዎችን በዝርዝር ያስቀምጣል። በዚህ መሠረት አንቀፅ 4 የአሳልፎ መስጠት ጥያቄን አለመቀበል የሚያስችሉ አስገዳጅ ምክንያቶችን (mandatory grounds for refusal) ሲዘረዝር ከነዚህም ውስጥ፣
• ጥያቄው በቀረበለት አገር የወንጀል ድርጊቱ ፖለቲካዊ ይዘት አለው ተብሎ ሲታመን፤
• ጥያቄው የቀረበለት አገር ጥያቄው የቀረበው ግለሰቡን በዘሩ፣ በኃይማኖቱ፣ በዜግነቱ፣ በጾታው፣ በፖለቲካ አመለካከቱ ወይም በመሰል ምክንያቶች ለመክሰስ መሆኑን በሚመለከት በቂ መረጃ ሲኖረው፤
• ጥያቄ የቀረበበት የወንጀል ድርጊት በወታደራዊ ወንጀልነት ብቻ የሚያስቀጣ ከሆነ
• ተላልፎ እንዲሰጥ ጥያቄው የቀረበበት ግለሰብ የአገራቱ ዜጋ ከሆነ
• የተጠየቀበት ወንጀል በቅርታ፣በምህረት ወይም በይርጋ ቀሪ ከሆነ
• የተጤቀዉን ጉዳይ በተመለከተ የተጠየቀዉ ሀገር በጉዳየ ላይ የመጨረሻ ፍርድ የሳረፈበትቨ ከሆነ
• ትብብሩን ማድረግ የጠጠየቂ ሀገርን ሉዓላዊነት፣ ደህንነት፣ ስርዓት እና ሌሎች መሰረታዊ ጥቅምን የሚጎዱ ከሆነ
ፈቃጅ የሆኑ መቃወሚያ መሰረቶች (Discretionary grounds of refusal) ደግሞ በአንቀጽ 5 ተዘርዝረዋል፡፡ እነሱም፡-
• ተጠያቂ ሀገር ጉዳዩን ለመመርመር ስልጣን ያለዉ ሲሆን እና ጉዳዩን መመርመር የጀመረ ወይም ምርመራ የጨረሰ ከሆነ
• ተጠያቂ ሀገር ጉዳዩ ላይ ምርመራ እንዳይደረግ ወይም የተጀመረ ምርመራ እንዲቋረጥ ከወሰነ
• የተፋለጊዉን የእድሜ፣ የጤና፣ የቤተሰብ ወይም ሌሎች ሁኔታዎችን ግምት ዉስት በማስገባት አሳልፎ መስጠት ከሰብዓዊነት አንፃር ተገቢ አይደለም ተብሎ በተጠያቂ ሃገር ሲታመን
• ተፈላጊዉ ላይ የተወሰነዉ ዉሳኔ በሌለበት ተወሰነ ከሆነና ዉሳኔዉ ተፈላጊዉ ተላልፎ ከተሰጠ በኋላ እሱ ባለበት ድጋሚ ሊታይ የሚችልበት እድል ከሌለ ናቸዉ፡፡
በስምምነቱ አንቀጽ 2 መሠረት የሚቀርቡ የአሳልፎ መስጠት ጥያቄዎችን ለማስተናገድ እንዲቻል በሀገራቱ መካከል የሚደረገው ግንኙነት በዲፕሎማሲያዊ መስመሩ መሆን እንዳለበት ያስቀመጠ ሲሆን በአገራችን በኩል የፍትሕ ሚኒስቴር በቱርክ በኩልም የፍትሕ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ማዕከላዊ ባለስልጣን (central Authorities) እንዲሆኑ ተሰይመዋል፡፡
በአንቀጽ 6 ትብብር የተጠየቀበት የወንጀል ድርጊት በሁለቱም ሀገር የወንጀል ህግጋት መሰረት በተመሳሳይ የሞት ቅጣት የማያስቀጣ ከሆነ ና በጠያቂ ሀገር ህግ በሞት ሊያስቀጣ የሚችል
ከሆነ ትብብር የተጠየቀ ሀገር የትብብር ጠያቂ ሃገር የሞት ቅታት ቢፈረድ እንኳን ቅጣቱ እንደማፈፀም ማረጋገጫ ካልሰጠ በቀር ትብብሩን አላደርግም ማለት እንደሚችል ተደንግጓል፡፡
አንቀፅ 7 በስምምነቱ በአንቀጽ 6፣ በአንቀጽ 4(መ) ዜግነትን መሰረት በማድረግ እና በ 5(ሐ) ከሰብዓዊነት አንፃር በማየት ትብብር ዉድቅ በሚደረግበት ጊዜ በጠያቂ ሀገር እንደገና ጠያቂነት ጉዳዩን በሀገራቸዉ የሚመለከተዉ አካል አይቶ ዉሳኔ እንዲሰጥበት የማድረግ ግዴታ ያለባቸዉ መሆኑን እና ይህንንም በተመለከተ ጠያቂ ሀገር ማስረጃዎችን እና ሰነዶችን ለተጠያቂ ሀገር ማስተላላፍ ለባት መሆኑ ይደነግጋል፡፡
በስምምነቱ አንቀጽ 8 አሳልፎ የመስጠት ጥያቄ በሚቀርብብት ጊዜ በፅሁፍ መቅረብ እንዳለበት እና ሲቀርብ ተያይዘው መቅረብ ስለሚገባቸው ሰነዶች ዝርዝር ተጠቅሷል። በዚህ መሠረት የጠያቂ እና የተጠያቂ ሀገራት ተቋም ስም፣ የግለሰቡን ማንነት በተሟላ ሁኔታ የሚገልጹ መረጃ ና ማስረጃዎች ( ስም፣ እድሜ፣ዜግነት፣ ስራ፣መኖሪያ፣ ተክለ ሰዉነት፣ ፎቶ ግራፍ፣ የጣት አሻራ)፣ አሳልፎ መስጠት የተጠየቀበት የወንጀል ዓይነት፣ ወንጀሉ የተፈጸመበት ጊዜና ቦታ፣ የወንጀል ድንጋጌዉንና ይርጋን በሚመለከት ያለዉን ህግ የሚያሳይ ገጽ ቅጅ፣ በጠያቂው አገር ፍርድ ቤት የወጣ የእስር ማዘዣ ዋናውና የተረጋገጠ ኮፒ ወይም የጥፋተኝነትና ቅጣት ውሣኔ፣ ተፈላጊዉ ቅታት ለማስፈፀም ሚፈለግ ከሆነ የቀረዉ የቅጣት ጊዜ የሚሉት ይገኙበታል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚቀርበው የአሳልፎ መስጠት ጥያቄ ጥያቄው በሚቀርብለት አገር የሥራ ቋንቋ ወይም በእንግሊዥኛ ቋንቋ ተተርጉሞ መቅረብ እንደሚኖርበት ተደንግጓል። በስምምነቱ አንቀጽ 9 መሰረት በአንቀጽ 8 ተዘረዘተሩት ማስረጃዎች እና መረጃዎች በበቂ ሁኔታ ካልቀረቡ ተጠያቂ ሀገር ለጠያቂ ሀገር ተጨማሪ ማስረጃ በ30 ቀናት ዉስጥ እንዲላክ ማሳወቅ እናዳለባት እና ጠያቂ ሀገር በተተቀሰዉ ጊዜ ማሟላት እንደሚጠበቅባት፤ ነገር ግን ይህን ማድረግ የማይቻልበት በቂ ምክንያት ካለ ተጨማሪ 15 ቀናት ዉስጥ መላክ እንዳለባቸዉ ተደንግጓል፡፡ በተተቀሰዉ ጊዜ ዉስት ተጨማሪ ማስረጃዉ እና መረጃዉ ለተጠያቂ ሀገር ከላተላከ ጠያቂ ሀገር ጥያቄዉን አንደተወችዉ ተቆጥሮ የታሰረ ተፈላጊ ካለም ጠያቂ ሀገርን በማሳወቅ ይለቀቃል፡፡ ነገር ግን አዲስ ጥያቄ በተመሳሳይ ጉዳይ እና በተመሳሳይ ግለሰብ ላይ ማቅረብን አይከለክልም፡፡
በስምምነቱ አንቀጽ 10 መሠረት አስቸኳይ ሁኔታ በሚፈጠርበት ጊዜ ጠያቂው አካል አሳልፎ የመስጠት ጥያቄ ከማቅረቡ በፊት በወንጀል የሚፈለገው ግለሰብ በጊዜያዊነት በቁጥጥር ሥር
እንዲውል በInterpol, በዲፕሎማሲያዊ መስመሩ ወይም ማእከላዊ ባለስልጣናቱ በሚስማሙበት ሌላ መስመር በኩል ሊጠይቅ እንደሚችል ተደንግጓል። ጥያቄዉ ሲቀርብም በአንቀጽ 8(1) (ሠ) ስር የተዘረዘሩት መረጃዎች መገለጽ ያለባቸዉ መሆኑን፣ በአንቀጽ 8(2) የተዘረዘሩት ማስረጃዎች ስለመኖራቸዉ መገለጽ ያለበት መሆኑን እና በቀጣይ መደበኛ የሆነ ጥያቄ እንደሚቀርብ መገለጽ እንዳለበት ተደንግጓል፡፡ ይህ ጥያቄ የደረሰዉ ሀገርም ወዲያዉኑ ምላሹን ማሳወቅ አለበት፡፡ መደበኛ ጥያቄዉም ተፈላጊዉ ከታሰረበት ቀን አንሰቶ በ 40 ቀናት ዉስጥ ካደረሰዉ ጥያቄው የቀረበለት ሀገር ተፈላጊዉን መልቀቅ ይችላል፡፡ ነገር ግን የ40 ቀን ጊዜዉ በጠያቂ ሀገር ማመልከቻ ለ 20 ቀናት ሊራዘም ይችላል፡፡ ነገር ግን የጊዜያዊ እስሩ መቋረጥ መደበኛ ጥያቄ ከቀረበ የአሳልፎ መስጠት ሂደትን አያቋርጠዉም፡፡
በስምምነቱ አንቀጽ 11 መሠረት ጥያቄው የቀረበለት ሀገር የሀገሩን ህግ መሰረት በማድረግ ጥያቄዉን ከመረመረ በኋላ ግለሰቡን አሳልፎ ለመስጠት ፈቃደኛ መሆን አለመሆኑን ለጠያቂ ሀገር ወዲያዉኑ መግለጽ እናዳለበት ተደንግጓል፡፡ የተወሰነዉ ዉሳኔ ጥያቄዉ በሙሉ ወይም በከፊል ዉድቅ እንዲሆን ከሆነ ምክንያቱን በመግለፅ ማሳወቅ እንዳለበት ተደንግጓል፡፡
በስምምነቱ አንቀፅ 12 መሰረት ተላልፎ እንዲሰጥ የተጠየቀበት ግለሰብ በራሱ ፈቃደኝነቱን በግልጽ ያሳወቀ እንደሆነ ተጠያቂ ሀገር የማስተላላፍ ሂደቱን ለማፋጠን የሚቻለዉን ሁሉ እንድታደርግ ግዴታ ተጥሎባታል፡፡
አንቀጽ 13 የሚደነግገዉ ተጠያቂ ሀገር ተፈላጊዉ ግለሰብ ተላልፎ እንዲሰጥ ከወሰነች በኋላ ግለሰቡ የሚተላለፍበትን ሂደት የሚያሳይ ሲሆን ግለሰቡ ተላልፎ በሚሰጥበት ጊዜ፣ ቦታ እና ሌሎች ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮች ላይ ሁለቱ ወገኖች በመመካከር መስማማት ላይ እንዲደርሱ የሚያስቀምጥ ሲሆን አሳልፎ የሚሰጠው አካል ተፈላጊው ግለሰብ ተላልፎ እንዲሰጥ በማሰብ ለምን ያህል ጊዜ በእስር ላይ እንደቆየ ለጠያቂው አካል የማሳወቅ ግዴታ እንዳለበትም ይደነግጋል፡፡ በዚህ መሠረት ጥያቄውን ያቀረበው አካል በተባለው ጊዜና ቦታ በመገኘት ግለሰቡን የመረከብ ግዴታ ያለበት ሲሆን ይህን ሳያደርግ ከቀረና ከተቆረጠው ጊዜ 30 ቀናት በላይ ካለፈ ግለሰቡን ሊለቅ እና ለወደፊት በዚሁ ግለሰብ ላይ በተመሳሳይ ጉዳይ ሚቀርብን የአሳልፎ የመስጠት ጥያቄውን ላለመቀበል እንደሚችል ተደንግጓል። ሆኖም ጥያቄውን ያቀረበው አካል ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት በተስማሙበት ጊዜ መረከብ የማይችልበት ሁኔታ ካጋጠመዉ
ከሆነ ይህንኑ ወዲያዉኑ ለተጠያቂ ሀገር በማሳወቅ በድጋሚ በርክክቡ ሂደት ላይ ሊስማማ ይችላሉ፡፡
በስምምነቱ አንቀጽ 14 ተላልፎ እንዲሰጥ የተጠየቀው ግለሰብ ጥያቄው በቀረበለት አገር ተላልፎ እንዲሰጥ ከተወሰነ በኋላ ተላልፎ የሚሰጠዉ ሰዉ ላይ የአሳልፎ መስጠት ጥያቄ ከቀረበበት ጉዳይ ዉጭ ሌላ የወንጀል ምርመራ እተከናወነበት፣ ክስ ተመስርቶበት ወይም ቅጣት ተላልፎበት እስሩን በመፈፀም ላይ የሚገኝ ከሆነ የማስተላለፍ ሂደቱ በትብብር ተጠያቂ ሀገር ዉሳኔ ላልተወሰነ ጊዜ ሊዘገይ ወይም ሊቆይ ስለሚችልበት ሁኔታ በአንቀጹ (1) ተደንግጓል፡፡ በተጨማሪም በአማራጭነት የማስተላላፉ መዘግየት በጠያቂ ሀገር ህግ መሰረት ጉዳዩ በይርጋ የሚያልፍ ወይም የምርመራዉን ሂደት የሚደናቅፍ ከሆነ በጠያቂው እና በተጠያቂው ሀገር መካከል በሚደረግ ስምምነት እና ቅድመ ሆኔታ መሰረት ተፈላጊውን በጊዜያዊነት ተላልፎ ሊሰጥ እንደሚችል ተደንግጓል። ተፈላጊዉ በጊዜያዊነት ተላፎ ተሰጠዉ ሀገርም በስምምነቱ መሰረት የሚፈለገዉን ሂደት ካጠናቀቀ በኋላ ተረፈላጊዉን ወደ ተጠያቂ ሀገር የመመለስ ግዴታ ተጥሎበታል፡፡
በስምምነቱ አንቀጽ 15 መሠረት የአሳልፎ መስጠት ጥያቄ ያቀረበው ሀገር ተላልፎ የተሰጠው ግለሰብ ከፈጸመው የወንጀል ድርጊት የተገኘን ንብረት ወይም ወንጀሉን ለመፈፀም ጥቅም ላይ የዋሉ ንብረቶችን ወይም በፍርድ ሂደት እንደማስረጃ ሊያገለግሉ የሚችሉ ንብረቶች እንዲሰጡት ጥያቄ ያቀረበ እንደሆነ ጥያቄው የቀረበለት ወገን የሀገሩ ሕግ በሚፈቅድለት መሰረት ለሌላኛው አሳልፎ መስጠት አለበት፡፡ ሆኖም ንብረቶቹ በተጠየቀው አገር የተጀመረ ሌላ የወንጀል የፍርድ ሂደት የሚፈለጉ ከሆነ ንብረቶቹን ማስረከቡን ለሌላ ጊዜ ሊያስተላልፍ ወይም እንዲመለሱለት በሚያቀርበው በቅድመ ሁኔታ ጠያቂው አገር ከተስማማ ለጊዜው አሳልፎ ሊሰጥ እንደሚችል ተመልክቷል፡፡ በተጨማሪም የንብረቶቹ መሰጠት የሶስተኛ ወገኖችን ጥቅም እና መብት መንካት እንደሌለበት ተደንግጓል፡፡
በስምምነቱ አንቀጽ 16 መሠረት ተላልፎ የተሰጠ ግለሰብ ተላልፎ ከተሰጠበት ወንጀል ውጪ በሌላ የወንጀል ጉዳይ ምክንያት ሊያዝ፣ ሊከሰስ ወይም ሊታሰር እንደማይችል እንዲሁም ለሦስተኛ አገር ተላልፎ ሊሰጥ እንደማይችል ተደንግጓል። ሆኖም ግለሰቡ ከጠያቂ አገር ወጥቶ በፈቃደኝነት ወደዛው ሀገር ከተመለሰ፣ ግለሰቡ ነፃ ከተደረገ በኋላ ከሀገሪቱ መዉጣት እየቻለ በ
45 ቀናት ውስጥ ከጠያቂ አገር ካልወጣ ወይም ጠያቂ ሀገር ለተጠያቂ ሀገር በአንቀጽ 8 የተዘረዘሩትን ተገቢ የሆኑ ሰነዶችና መረጃዎችን በመሟላት የተጠያቂ አገርን ፈቃድ በመጠየቅ ተጠያቂ ሀገር ከተስማማች ከላይ የተቀመጠው ግዴታ ተፈጻሚ አይደረግም።
በስምምነቱ አንቀጽ 17 ላይ ከሌላ ሦስተኛ ሀገር ተላልፎ ለአንደኛው ወገን የተሰጠ ተፈላጊ በሌላኛው ግዛት ውስጥ እንዲተላለፍ የትብብር ጥያቄ ሲቀርብ ከአገራቱ ሕግ ጋር የማይቃረንና መሆኑን በማረጋገጥ ተፈላጊው እንዲያልፍ መፍቀድ እንዳለባቸው ሆኖም የመተላላፍ ሂደቱ በአዉሮፕላን ከሆነ እና አዉሮፕላኑ በጠያቂ ሀገር የግዛት ክልል ዉስጥ እንደሚያርፍ ቀድሞ ያልታቀደ ከሆነ ጥያቄ ማቅረብ አያስፈልግም፡፡ ጥያቄ ማቅረብ በሚያስፈልግበት ጊዜ የሚተላለፈዉ ግለሰብ ማንነት ዜግነቱን ጨምሮ፣ የመያዣ ትዕዛዝ ወይም ፍርድ ካለ ኮፒዉን
፣ የወንጀሉ ዝርዝር እና ተፈጻሚነት ያለዉን የህግ ክፍል ቅጅ ሚያሳዩ መረጃዎች እና ማስረጃዎች ከጥያቄዉ ጋር አብረዉ መላከ ያለባቸዉ መሆኑ ተደንግጓል፡፡
በስምምነቱ አንቀጽ 18 ላይ ደግሞ ተላልፎ የተሰጠን ሰው በሚመለከት ግለሰቡን አሳልፎ ለሰጠው ወገን የጉዳዩን ውጤት አስምልከቶ በስድስት ወር ጊዜ ዉስጥ የማሳወቅ ግዴታ እንዳለበት ተቀምጧል።
በስምምነቱ አንቀጽ 19 ላይ ተመሣሣይ የአሳልፎ መስጠት ጥያቄ በተመሳሳይ ሰው ላይ ከስምምነቱ አባል ሀገር ተጨማሪ በሌላ ሀገር ሲቀርብ በተጠያቂ ሀገር ጥያቄው ስለሚስተናገድበት አግባብ ሲያስቀምጥ ሁሉንም ከባቢያዊ ሁኔታዎች በተለይም የወንጀሉ ክብደት፣ ወንጀሉ የተፈፀመበት ቦታ፣ ጥያቄዉ የቀረበበትን ጊዜ፣ የተፈላጊው ግለሰብ እና የወንጀል ተጎጂ/ዎችን ዜግነት እና ተላልፎ ከተሰተ በኋላ ለሶስተኛ ወገን ተላልፎ የመሰጠት ዕድል እንዲሁም የወንጀሉ ተጠቂዎች ዜግነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ወደየትኛው ሀገር ተላልፎ እንደሚሰጥ ግምት ዉስጥ በማስገባት ለመወሰን የሚችል ስለመሆኑ ያስረዳል፡፡ ይህንንም ዉሳኔዉን ለስምምነቱ አባል ሀገር የማሳወቅ ግዴታን ይጥላል፡፡
የስምምነቱ አንቀጽ 20 ከስምምነቱ አተገባበር ጋር ተያይዞ የሚመጡ ወጪዎችን የሚመለከት ሲሆን በዚህ መሠረት ጥያቄው የቀረበለት አካል አሳልፎ ከመስጠት ጥያቄው ጋር ተያይዞ በአገሩ የሚያወጣውን ወጪ፣ ተላልፎ የሚሰጠውን ግለሰብ በአገሩ ለመያዝ የሚያወጣውን ወጪ እና ተላልፎ ከሚሰጠው ግለሰብ ጋር አብሮ ተይዞ ለሚተላለፍ ወንጀሉን ለመፈፀም ጥቅም ላይ የዋለ ንብረትን ለመያዝና ለማስተላለፍ የሚያወጣውን ወጪ እንደሚሸፍን
ተደንግጓል። ጥያቄውን ያቀረበው ሀገር በበኩሉ ተላልፎ የሚሰጠውን ግለሰብ እና ንብረት ወደ አገሩ ለማጓጓዝ የሚያስፈልገውን ወጪ እንደሚሸፍን ተደንግጓል።
በስምምነቱ አንቀጽ 21 ተዋዋይ ሀገራት ይህ ስምምነት ተፈፃሚ በሚሆንበት ጊዜ አንዳቸዉ ከሌላቸዉ የሚያገኙትን ማንኛዉንም መረጃ ስምምነቱ ተግባራዊ በሚሆንበት ጊዜም ሆነ ቀሪ ከሆነ በኋላ ያለሌላኛዉ ወገን ፈቃድ ለሶስተኛ ሀገር ያለመግለፅ እና ጥበቃ ለማድረግ ተስማምተዋል፡፡
አንቀጽ 22 ስምምነቱ ሁለቱም ሀገራት በሌላ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የሚያገኙትን ማንኛዉንም መብት ሆነ የተጣለባቸዉን ግዴታ ሊያቀር የማይችል መሆኑን ሲደነግግ አንቀጽ
23 ደግሞ በስምምነቱ አፈፃፀምም ሆነ አተረጓጎም ላይ በሁለቱም ሀገራት ማዕከላዊ ባለስልጣናት የሚነሱ አለመግባባቶች በዲፕሎማሲያዊ መስመር በሚደረግ ምክክር እንደሚፈቱ ይደነግጋል፡፡
የስምምነቱ አንቀጽ 24 የመጨረሻ ድንጋጌዎችን የያዘ ሲሆን ስምምነቱ ወደ ሥራ የሚገባው በሁለቱም ሀገራት መጽደቁን በሚመለከት ሰነድ በዲፕሎማቲክ መስመር ልውውጥ በተደረገበት ቀን እንደሆነ ተደንግጓል። በተጨማሪም ሀገራቱ የ180 ቀናት የጽሑፍ ቅድመ-ማስታወቂያ በመስጠት የስምምነቱን ተፈጻሚነት ቀሪ ማድረግ እንደሚችሉ ተደንግጓል። ይህም ቀድሞ የተጀመሩ የአሳልፎ መስጠት ሂደቶች ላይ የሚስከትለዉ ተጽዕኖ የሌለ መሆኑ ተደንግጓል፡፡ በመጨረሻም ስምምነቱ ወደ ስራ ከገባበት ጊዜ በፊት የተፈፀሙ ወንጀሎችን ጨምሮ በሀገራቱ በሚቀርቡ ማንኛዉም የአሳልፎ መስጠት ጥያቄዎች ላይ ተፈፃሚ እንደሚደረጉ ተደንግገዋል፡፡
6. ማጠቃለያ
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት እና በተርክየ ሪፐብሊክ መንግስት መካከል በወንጀል ጉዳይ ግለሰቦችን አሳልፎ መስጠትን አስመልክቶ የተደረገው ስምምነት በሁለቱ አገሮች ሰላምን፣ ፀጥታን እና መረጋጋትን ለማረጋገጥ አስተዋፅኦ የሚያደርግ የትብብር ማዕቀፍን የሚፈጥር በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ እንደሚሆን ይታመናል። ማንኛውም ወንጀልን የፈጸመ ግለሰብ ለፍትሕ መቅረብ ያለበት በመሆኑና ወንጀልን ፈጽሞ ወደሌላ አገር በመሸሸጉ ከተጠያቂነት ሊያመልጥ የማይገባ ስለሆነ አሳልፎ የመስጠት ስምምነቱን ተግባራዊ ማድረጉ
ጠቃሚ እንደሚሆን ይታመናል። ከዚህ አንጻር በሚኒስትሮች ምክር ቤት እና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውይይት ተደርጎበት እንዲጸድቅ ረቂቅ አዋጁን አያይዘን አቅርበናል።
አዋጅ ቁጥር /2015
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት እና በቱርከ ሪፐብሊክ መንግስት መካከል የተደረገውን የአሳልፎ መስጠት ስምምነት ለማጽደቅ የወጣ አዋጅ
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት እና በቱርክ ሪፐብሊክ መንግስት መካከል የተደረገውን የአሳልፎ መስጠት ስምምነት እ.ኤ.አ. ግንቦት 10 ቀን 2022 በአንካራ የተፈረመ በመሆኑ፤
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 55 ንዑስ አንቀጽ (1) እና (12) መሠረት የሚከተለው ታውጇል፡፡
1. አጭር ርዕስ
ይህ አዋጅ “በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት እና በቱርክ ሪፐብሊክ መንግስት መካከል የተደረገውን የአሳልፎ መስጠት ስምምነት ማጽደቂያ አዋጅ ቁጥር..../2015” ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡
2. ስምምነቱ ስለመጽደቁ
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት እና በቱርክ ሪፐብሊክ መንግስት መካከል እ.ኤ.አ. ግንቦት 10 ቀን 2022 በአንካራ የተፈረመው የአሳልፎ መስጠት ስምምነት ፀድቋል፡፡
3. የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የፍትሕ ሚኒስቴር ኃላፊነት
የኢፌዴሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ይህን ስምምነት ለማስፈጸም አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎችን ሁሉ እንዲወስድ በዚህ አዋጅ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡
4. አዋጁ የሚፀናበት ጊዜ
ይህ አዋጅ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ የፀና ይሆናል:: አዲስ አበባ..... ቀን ዓ.ም.
ሳህለወርቅ ዘዉዴ
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት
Proclamation No /2022
A PROCLAMATION TO RATIFY THE EXTRADITION TREATY BETWEEN THE GOVERNMENT OF THE FEDERAL DEMOCRATIC REPUBLIC OF
ETHIOPIA AND THE GOVERNMENT OF THE REPUBLIC OF TURKIYE
WHEREAS the Extradition Treaty between the Government of the Federal Democratic Republic of Ethiopia and the Government of the Republic of Turkiye has been signed in Ankara, on the 10 May, 2022;
NOW, THEREFORE, in accordance with sub-articles (1) and (12) of Article 55 the Constitution of the Federal Democratic Republic of Ethiopia, it is hereby proclaimed as follows:
1. Short Title
This Proclamation may be cited as the “Extradition Treaty between the Government of the Federal Democratic Republic of Ethiopia and the Government of the Republic of Turkiye Ratification Proclamation No…/2022”.
2. Ratification of the Agreement
The Extradition Treaty signed in Ankara on the 10 May 2022 between the Government of the Federal Democratic Republic of Ethiopia and the Government of the Republic of Turkiye, is hereby ratified.
3. Responsibility of the FDRE Ministry of Justice
The FDRE Ministry of Justice is hereby empowered to undertake all acts necessary for the implementation of the Treaty.
4. Effective Date
This Proclamation shall come into force on the date of its publication in the Federal Negarit Gazeta.
Done at Addis Ababa on this ….day of .….in the Year 2022
Sahilework Xxxxxx
PRESIDENT OF THE FEDERAL DEMOCRATIC REPUBLIC OF ETHIOPIA