Contract
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት እና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መንግስት መካከል የተደረገውን የአሳልፎ መስጠት ስምምነት
ለማፀደቅ የተዘጋጀ ማብራሪያ
ጥር 2015
1. መግቢያ
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት እና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መንግስት መካከል እ.ኤ.አ. ሴፕምበር 21 ቀን 2022 በወንጀል ጉዳይ የሚፈለጉ ግለሰቦችን አሳልፎ የመስጠት ስምምነት በአቡዳቢ ተፈርሟል። በስምምነቱ መግቢያ ላይ ስምምነቱ ወንጀልን በመከላከል እና የወንጀል ስነ-ስርዓት ሂደትን በተመለከተ ዓለም አቀፍ አሰራርን መሰረት ያደረገ ዉጤታማ የሆነ የወንጀል መከላከል ትብብር ለማድረግ ታስቦ የተፈረመ ስምምነት መሆኑን ይገልፃል፡፡
ስለሆነም ስምምነቱ በወንጀል ጉዳይ የሚፈለጉ ተጠርጣሪ ወይም ፍርደኞችን አሳልፎ በመስጠት ረገድ ለሚደረገው የሁለትዮሽ ትብብር የሕግ ማዕቀፍን የሚፈጥር በመሆኑ በሚኒስትሮች ምክር ቤት እና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውይይት ተደርጎበት እንዲጸድቅ ለማስቻል ይህ መግለጫ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡
2. ስምምነቱ በአገራችን ላይ የሚጥለዉ ግዴታ
ስምምነቱ በወንጀል ጉዳዮች ግለሰቦችን አሳልፎ ለመስጠት የተደረገ ስምምነት እንደመሆኑ በአገራችን ላይ የሚጥላቸው ልዩ ልዩ ግዴታዎች አሉ። ከእነዚህ መካከልም ዋነኛው በተባበሩት የአረብ ኤምሬቶች መንግስት በሚቀርብ ጥያቄ መሠረት አሳልፎ ለመስጠት በሚያበቃ የወንጀል ድርጊት ምክንያት ለክስ ወይም ቅጣት እንዲፈጸምበት የሚፈለግን በአገራችን የሚገኝ ግለሰብ አሳልፎ የመስጠት ግዴታ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ ተላልፎ የሚሰጠውን ግለሰብ በአገር ውስጥ ለመያዝ የሚወጣው ወጪ እና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ተላልፎ የሚሰጠው ግለሰብ ወንጀሉን ለመፈፀም የተጠቀመበትን ንብረት ለመያዝና ለማስተላለፍ የሚያስፈልገውን ወጪ በአገራችን በኩል እንዲሸፈን ግዴታን ይጥላል። ነገር ግን ተፈላጊዉን ወደ ተባበሩት የአረብ ኤምሬቶች ለማጓጓዝ የሚያስፈልግ የትራንስፖርት ወጭን አይጨምርም፡፡
በሌላ በኩል በስምምነቱ አንቀጽ 13 መሠረት አስቸኳይ ሁኔታ በሚፈጠርበት ጊዜ አሳልፎ የመስጠት ጥያቄ ከመቅረቡ በፊት በወንጀል የሚፈለገው ግለሰብ በጊዜያዊነት በቁጥጥር ሥር እንዲውል የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ወገን በሚጠየቅበት ጊዜ የጉዳዩን አግባብነት ተገንዝቦ ተፈጻሚ ማድረግ አስፈላጊ ሲሆን ተፈላጊዉን የመያዝ እና እስከ 45(አርባ አምስት) ቀናት የማቆየት ግዴታ በሀገራችን ላይ ይጥላል፡፡
ሆኖም በአጠቃላይ የትብብር ስምምነቱ ተፈጻሚነት በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ በተባበሩት የአረብ ኤምሬቶች መንግስት የሚቀርብን ጥያቄ በአገራችን የሚስተናገደው በአገራችን በኩል ለተባበሩት የአረብ ኤምሬቶች መንግስት የሚቀርብ ጥያቄ በሚስተናገድበት አግባብ ይሆናል።
3. የስምምነቱ መጽደቅ ለአገራችን የሚኖረዉ ጠቀሜታ
ሀገራችን በምታደርገዉ የልማት እና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አጠናክሮ ለማስቀጠል ጉልህ ሚና ከሚጫወቱ ነገሮች መካከል የሕግ የበላይነት መከበር ነው፡፡ የዚህም አንዱ መገለጫ ወንጀል ፈፅመው ከሀገር የሚሸሹ ወንጀለኞችን ለፍርድ የማቅረብ ሂደት ሲሆን ይህንንም ለማከናወን በእንካ ለእንካ መርህ መሰረት ከሚካሄዱ ትብብሮች በተጨማሪ በሀገራት መካከል ስምምነቶችን መፈራረም እና ፀድቀው ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረግ ዋናው እና የተሻለዉ የትብብር መሰረት ነው፡፡
የተባበሩት የአረብ ኤምሬቶች እና ኢትዮጵያ ያላቸዉ ግንኙነት ለረጅም ጊዜ የነበረ እና በተለይም ደግሞ በአሁኑ ሰዓት ዘርፈ ብዙ እና ከዕለት ወደ ዕለት እያደገ መምጣቱ ይታወቃል፡፡ በተለይም በንግድ እና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ያላቸዉ ግንኙነት እየጨመረ የመጣ በመሆኑ እና በዚህም ምክንያት ኢትጵያውያን በቀላሉ ወደ ተባበሩት የአረብ ኤምሬቶች መጓዝ መቻላቸው ወንጀለኞችም ይህንን ሁኔታ በመጠቀም ከሕግ ለማምለጥ ወደ ተባበሩት የአረብ ኤምሬቶች ለመሄድ የሚችሉበት አጋጣሚ ሰፊ ነዉ፡፡ ይህም በተጨባጭ ከዚህ በፊት በተለያ ጊዜያት አጋጥሞናል፡፡ ለምሳሌ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወርቅ በማጭበርበር የዘረፈ ግለሰብ ወደ ዱባይ በመሄድ ለማምለጥ የሞከረበት እና ሌሎች ወደዛዉ ሸሽተዋል ተብለዉ በተለያዩ ወንጀሎች የሚፈለጉ ሰዎች እንዳሉ ማዉሳት ይቻላል፡፡ በመሆኑም ይህን ተከትለው የሚመጡ የአሳልፎ መስጠት ትብብር ጉዳዮችን በሕግ ማዕቀፍ ምላሽ ለመስጠት ስምምነቱ አስፈላጊ እንደሆነ ይታመናል፡፡
4. የስምምነቱ አፈጻጸም
የስምምነቱን አፈጻጸም በሚመለከት የተቀመጡትን ድንጋጌዎች ለማስፈጸምና ተፈጻሚነታቸውን ለመከታተል ኃላፊነቱን የሚወስድ መንግስታዊ አካል መሰየም አስፈላጊ መሆኑ ይታወቃል። ከዚህ አንፃር የስምምነቱ ይዘት በወንጀል ጉዳዮች ወንጀለኞችን አሳልፎ መስጠትን የሚመለከት በመሆኑ የወንጀል ጉዳዮች ትብብር አካል ነዉ። በዚህ ረገድ የፌዴራል አስፈፃሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣዉ አዋጅ ቁጥር 1263 አንቀጽ 40(1) እና የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግን ለማቋቋም የወጣው አዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀጽ 6 (12) ) መሠረት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር በወንጀልና በፍትሐብሔር ጉዳዮች ዓለም አቀፍ ግንኙነትና ትብብር እንዲያደርግ ኃላፊነት የተጣለበት በመሆኑ እንዲሁም በስምምነቱ አንቀጽ 7 መሠረት የስምምነቱን አተገባበር ለመከታተል የፍትሕ ሚኒስቴር እንደ ማዕከላዊ ባለስልጣን የተሰየመ በመሆኑ ይህንን ስምምነት ለማስፈጸምና ተፈፃሚነቱን ለመከታተል ኃላፊነት ይኖረዋል፡፡
5. የስምምነቱ ይዘት
ስምምነቱ በይዘት ረገድ የስምምነቱ ዓላማ፣አሳልፎ ስለመስጠት ግዴታ፣ አሳልፎ ለመስጠት ስለሚያበቁ የወንጀል ድርጊቶች (Extraditable Offences)፣ አሳልፎ የመስጠት ጥያቄ ውድቅ ሊደረግ ስለሚችልባቸዉ ሁኔታዎች፣ የትብብር ጥቄዉ የሚላክለት አካል ፣ አሳልፎ የመስጠት ጥያቄ ስለሚስተናገድበት ሥነ-ሥርዓት እንዲሁም ሌሎች ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችን የያዙ ሃያ አራት
(24) አንቀጾች አሉት።
በስምምነቱ አንቀጽ 1 የስምምነቱ ዓላማ የተገለፀ ሲሆን ስምምነቱን መሰረት በማድረግ በሁለቱ አባል ሀገራት መካከል በአሳልፎ መስጠት ዙሪያ የሚደረግ ትብብርን መሳደግን ዓላማ ያደረገ ስምምነት መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በስምምነቱ አንቀጽ 2 መሠረት ሀገራቱ በጠያቂ ሀገር የወንጀል ድርጊት ክስ ሊቀርብበት፣ ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ወይም ቅጣት እንዲፈጸምበት የሚፈለግን ግለሰብ ስምምነቱን መሰረት በማድረግ አሳልፎ ለመስጠት ግዴታ ገብተዋል።
ስምምነቱ አንቀጽ 3 መሰረት አሳልፎ ለመስጠት የሚያበቃ የወንጀል ድርጊቶች ማለት አሳልፎ የመስጠት ጥያቄው በቀረበበት ጊዜ በሁለቱም አገራት ሕግ ቢያንስ በአንድ ዓመት ቀላል እስራት ሊያስቀጣ የሚችል የወንጀል ድርጊት መሆኑን አስቀምጧል። ሆኖም አሳልፎ የመስጠት ጥያቄው
የቀረበው በፍርድ ቤት የተላለፈ የቅጣት ውሣኔን ለማስፈጸም በሚሆንበት ጊዜ ቀሪው የቅጣት ጊዜ ቢያንስ ስድስት ወር ሊሆን እንደሚገባ ተደንግጓል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የአሳልፎ መስጠት ጥያቄው የሚቀርብለት አካል የወንጀሉን ዓይነት ሲመረምር በጠያቂው ሀገር ሕግ አገላለፅ እና በተጠያቂው ሀገር ህግ አገላለፅ ልዩነት መኖሩ ወይም ወንጀሎቹ የሚመደቡበት ክፍል (category of offences) የተለያየ መሆኑ ልዩነት እንደማይፈጥር ያስቀምጣል፡፡ ከአንድ በላይ በሆኑ ወንጀሎች የሚፈለግ ግለሰብን በተመለከተ ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ከተጠየቁት የወንጀል ጉዳዮች መካከል አንዱ ብቻ ተላልፎ ለመስጠት የሚያበቃ ወንጀል ከሆነ ሌሎቹ ባይሆኑም እንኳን አንዱ በመሆኑ ምክንያት በሁሉም ወንጀል ጉዳዮች ተላልፎ እንዲሰጠ ተደንግጓል፡፡
የስምምነቱ አንቀጽ 4 እና 5 አሳልፎ የመስጠት ጥያቄ ውድቅ ሊደረግ የሚችልባቸውን ሁኔታዎችን በዝርዝር ያስቀምጣል። በዚህ መሠረት አንቀፅ 4 የአሳልፎ መስጠት ጥያቄን አለመቀበል የሚያስችሉ አስገዳጅ ምክንያቶችን (mandatory grounds for refusal) ሲዘረዝር ከነዚህም ውስጥ፣
• ጥያቄው በቀረበለት አገር የወንጀል ድርጊቱ ፖለቲካዊ ይዘት አለው ተብሎ ሲታመን፤
• ጥያቄው የቀረበለት አገር ጥያቄው የቀረበው ግለሰቡን በዘሩ፣ በኃይማኖቱ፣ በዜግነቱ፣ በጾታው፣ በፖለቲካ አመለካከቱ ወይም በመሰል ምክንያቶች ለመክሰስ መሆኑን በሚመለከት በቂ መረጃ ሲኖረው፤
• ጥያቄ የቀረበበት የወንጀል ድርጊት በወታደራዊ ወንጀልነት ብቻ የሚያስቀጣ ከሆነ
• የተጠየቀዉን ጉዳይ በተመለከተ የተጠየቀዉ ሀገር በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ ፍርድ የተላለፈበት ከሆነ
• የተጠየቀበት ወንጀል በቅርታ፣በምህረት ወይም በይርጋ ቀሪ ከሆነ
• ተፈላጊዉ ተላልፎ ከተሰተ በኋላ የማሰቃት ተግባር ወይም ጭካኔ የተሞላበት፣ ኢሰብዓዊ የሆነ ወይም ክብሩን የሚያዋርድ አያያዝ ሊያጋጥመዉ የሚችል ከሆነ
• ተፈላጊዉ ላይ የተወሰነዉ ዉሳኔ በሌለበት ተወሰነ ከሆነና ዉሳኔዉ ተፈላጊዉ ተላልፎ ከተሰጠ በኋላ እሱ ባለበት ድጋሚ ሊታይ የሚችልበት እድል ከሌለ
• ተፈላጊዉ ሰዉ በተመሳሳይ ጉዳይ በሌላ ሀገር ተከሶ በነፃ የተሰናበተ፣ በይቅርታ የታለፈ ወይም ተቀጥቶ ቅጣቱን በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ የፈፀመ ከሆነ ናቸዉ፡፡
የፖለቲካ ወንጀልነትን የመወሰን ስልጣን የትብብር ተጠያቂ ሀገር ሲሆን በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በኩል በፕሬዝዳንቱ፣በምክትል ፕሬዝዳንቱ፣ በጠቅላይ ሚኒስቴሩ፣ በማንኛዉም
የፌዴራል ጠቅላይ ምክር ቤት (Federal Suprem Council) አባል እና በቤተሰቦቻቸዉ ላይ የተሰነዘረ ጥቃት፤ በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ በማንኛዉም ሰዉ፣ በመንግስት ኃላፊዎች እና በቤተሰቦቻቸዉ በህይወታቸዉ እና በደህንነታቸዉ ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች እንደ ፖለቲካ ወንጀሎች የማይቆጠሩ ሲሆን በተጨማሪም በሌሎች ሀገሮቹ አባል በሆኑባቸዉ የባለ ብዙ ወገን ስምምነቶች መሰረት እንደ ፖለቲካ ወንጀል የማይቆጠሩ ወንጀሎች፣ የሰዉ መግደል ወንጀል፣ ሽብርተኛነት እና በነዚህ ወንጀሎች ማሴር፣ ሙከራ ማድረግ እና ወንጀለኛን በመርዳት መሳተፍ ወንጀሎች እንደ ፖለቲካ ወንጀሎች አይቆጠሩም፡፡
ፈቃጅ የሆኑ መቃወሚያ መሰረቶች (Discretionary grounds of refusal) ደግሞ በአንቀጽ 5 ተዘርዝረዋል፡፡ እነሱም፡-
• ተጠያቂ ሀገር ጉዳዩ ላይ ምርመራ እንዳይደረግ ወይም የተጀመረ ምርመራ እንዲቋረጥ ከወሰነ
• ተጠያቂ ሀገር ጉዳዩን መመርመር የጀመረ ወይም ምርመራ የጨረሰ ከሆነ
• በተጠያቂ ሀገር ህግ መሰረት ወንጀሉ በተጠያቂ ሀገር ዉስጥ በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ እንደተፈፀመ የሚቆጠር ከሆነ
• የተፈፀመወን ወንጀል አደገኝነት፤ የተፋለጊዉን የእድሜ፣ የጤና፣ የቤተሰብ ወይም ሌሎች ሁኔታዎችን ግምት ዉስጥ በማስገባት አሳልፎ መስጠት ከሰብዓዊነት አንፃር ተገቢ አይደለም ተብሎ በተጠያቂ ሃገር ሲታመን
በስምምነቱ አንቀጽ 6 መሰረት ተፋላጊዉ ሰዉ የተጠያቂ ሀገር ዜግነት ያለዉ ከሆነ አሳልፎ ያለመስጠት መብት እንዳላቸዉ፡፡ ነገር ግን ተፈላጊዉን ሰዉ የሀገራቸዉ ህግ በሚፈቅደዉ መሰረት ለህግ ማቅረብ እናዳለባቸዉ ሲደነግግ፡፡ የትብብር ጠያቂ ሀገር አስፈላጊ የሆኑ ሰነዶችን እና መስረጃዎችን ለተጠያቂነሀገር የማስጠት እና ተጠያቂ ሀገርም ለጠያቂ ሀገር የተወሰደዉን እርምጃዎች ስትጠየቅ የማሳወቅ ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡
በስምምነቱ አንቀጽ 7 መሠረት የሚቀርቡ የአሳልፎ መስጠት ጥያቄዎችን ለማስተናገድ እንዲቻል በሀገራቱ መካከል የሚደረገው ግንኙነት በጽሁፍ መሆን እንዳለበት ያስቀመጠ ሲሆን በአገራችን በኩል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ (የፍትሕ ሚኒስቴር) በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በኩልም የፍትሕ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ማዕከላዊ ባለስልጣን (central Authorities) እንዲሆኑ ተሰይመዋል፡፡ የሚቀርቡ የአሳልፎ መስጠት ጥያቄዎችን ለማስተናገድ እንዲቻል በሀገራቱ መካከል የሚደረገው ግንኙነት በዲፕሎማሲያዊ መስመሩ መሆን እንዳለበት ያስቀመጠ ሲሆን ነገር ግን አስቸኳይ
ሁኔታዎች ሲያጋጥም በቀጥታ ማዕላዊ ባለስልጣናቱ መገናኘት እንደሚችሉ እና መደበኛ የሆነ ጥያቄ በ45 ( አርባ አምስት) ቀናት መቅረብ እንዳለበት ተደንግጓል፡፡
በአንቀጽ 8 ትብብር የተጠየቀበት የወንጀል ድርጊት በጠያቂ ሀገር የወንጀል ህግ መሰረት የሞት ቅጣት የሚያስቀጣ ከሆነ ትብብር የተጠየቀ ሀገር የትብብር ጠያቂ ሃገር የሞት ቅጣት ቢፈረድ እንኳን ቅጣቱ እንደማፈፀም ማረጋገጫ ካልሰጠ በቀር ትብብሩን አላደርግም ማለት እንደሚችል ተደንግጓል፡፡
በስምምነቱ አንቀጽ 9 አሳልፎ የመስጠት ጥያቄ በሚቀርብብት ጊዜ በፅሁፍ ሆኖ በዲፕሎማሲያዊ መስመር መቅረብ እንዳለበት እና ሲቀርብ ተያይዘው መቅረብ ስለሚገባቸው ሰነዶች ዝርዝር ተጠቅሷል። በዚህ መሠረት የግለሰቡን ማንነት በተሟላ ሁኔታ የሚገልጹ መረጃ ና ማስረጃዎች ( ስም፣ እድሜ፣ዜግነት፣ ስራ፣መኖሪያ፣ ተክለ ሰዉነት፣ ፎቶ ግራፍ፣ የጣት አሻራ)፣ አሳልፎ መስጠት የተጠየቀበት የወንጀል ዓይነት፣ ወንጀሉ የተፈጸመበት ጊዜና ቦታ፣ የወንጀል ድንጋጌዉንና ይርጋን በሚመለከት ያለዉን ህግ የሚያሳይ ገጽ ቅጅ፣ በጠያቂው አገር ፍርድ ቤት የወጣ የእስር ማዘዣ፣ተፈላጊዉ የተቀጣዉ በሌለበት ከሆነ በወቅቱ አስፈላጊዉ ጥሪ እና ማስታወቂያ የተደረገበት ሰነድ ኮፒ፣ የምስክሮች ቃል ኮፒ ወይም የጥፋተኝነት ወይም እና ቅጣት ውሣኔ፣ ተፈላጊዉ ቅጣት ለማስፈፀም ሚፈለግ ከሆነ የቀረዉ የቅጣት ጊዜ የሚሉት ይገኙበታል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚቀርበው የአሳልፎ መስጠት ጥያቄ ጥያቄው በሚቀርብለት አገር የሥራ ቋንቋ ወይም በእንግሊዥኛ ቋንቋ ተተርጉሞ መቅረብ እንደሚኖርበት ተደንግጓል።
በስምምነቱ አንቀፅ 10 ተላልፎ እንዲሰጥ የተጠየቀበት ግለሰብ በራሱ ፈቃደኝነቱን በግልጽ ለመተላለፍ ፈቃደኝነቱን ያሳወቀ እንደሆነ በአንቀፅ 9 ተዘረዘሩት ማስረጃወች እንዲቀርቡ ሳያስፈልጉ የቀረበን የጊዜያዊ አስር ማመልከቻ መሰረት በማድረግ ተላልፎ ሊሰጥ እንዲሚቻል ሲደነግግ፤ነገር ግን ተጠያቂ ሀገር ተጨማሪ መረጃዎችን መጠየቅ እንደሚችል ተደንግጓል፡፡ ለመተላለፍ የሚሰጥ የተፈላጊዉ ሰዉ ፈቃድ ተቀባነት የሚኖረዉ በህግ ባለሙያ ተደግፎ በተጠያቂ ሀገር አግባነት ያለዉ አካ ፊት በመቅረብ መደበኛ የሆነ የአሳልፎ መስጠት ጥያቄ ቀርቦ፣ የተገዳቢነት መርህ ተጋባራዊ እንደሚደረግ ተገልፆለት እና የሰጠዉ ፈቃድ የማይለወጥ መሆኑን ተነግሮት መሆን አለበት፡፡ በተጨማሪም በዚህ መሰረት የተሰጠ ፈቃድ ህጋዊ በሆነ መንገድ ተመዝግቦ ሪፖርት መደረግ አለበት፡፡
በስምምነቱ አንቀጽ 11 መሠረት ጥያቄው የቀረበለት ሀገር የሀገሩን ህግ መሰረት በማድረግ ጥያቄዉን ከመረመረ በኋላ ግለሰቡን አሳልፎ ለመስጠት ፈቃደኛ መሆን አለመሆኑን ለጠያቂ ሀገር ወዲያዉኑ መግለጽ እንዳለበት ተደንግጓል፡፡ የተወሰነዉ ዉሳኔ ጥያቄዉ በሙሉ ወይም በከፊል ዉድቅ እንዲሆን ከሆነ ምክንያቱን በመግለፅ ማሳወቅ እንዳለበት ተደንግጓል፡፡
በስምምነቱ አንቀጽ 12 መሰረት ከአሳልፎ መስጠት ጥያቄዉ ጋር ተያዘዉ የቀረቡት ማስረጃዎች እና መረጃዎች በቂ ካልሆኑ ተጠያቂ ሀገር ለጠያቂ ሀገር ተጨማሪ ማስረጃ በ30 (በሰላሳ) ቀናት ዉስጥ እንዲላክ ማሳወቅ እናዳለባት እና ጠያቂ ሀገር በተጠቀሰዉ ጊዜ ማሟላት እንደሚጠበቅባት፤ ነገር ግን ይህን ማድረግ የማይቻልበት በቂ ምክንያት ካለ በሚስማሙት ተጨማሪ ቀናት ዉስጥ ለመላክ እንዳለባቸዉ ተደንግጓል፡፡ በተጠቀሰዉ ጊዜ ዉስጥ ተጨማሪ ማስረጃዉ እና መረጃዉ ለተጠያቂ ሀገር ካልተላከ ጠያቂ ሀገር ጥያቄዉን አንደተወ ይቆጠራል፡፡ ነገር ግን አዲስ ጥያቄ በተመሳሳይ ጉዳይ እና በተመሳሳይ ግለሰብ ላይ ማቅረብን አይከለክልም፡፡
በስምምነቱ አንቀጽ 13 መሠረት አስቸኳይ ሁኔታ በሚፈጠርበት ጊዜ ጠያቂው አካል አሳልፎ የመስጠት ጥያቄ ከማቅረቡ በፊት በወንጀል የሚፈለገው ግለሰብ በጊዜያዊነት በቁጥጥር ሥር እንዲውል በInterpol, በዲፕሎማሲያዊ መስመሩ ወይም ማእከላዊ ባለስልጣናቱ በሚስማሙበት ሌላ መስመር በኩል ሊጠይቅ እንደሚችል ተደንግጓል። ጥያቄዉ ሲቀርብም በአንቀጽ 9(2) ስር የተዘረዘሩት መረጃዎች መገለጽ ያለባቸዉ መሆኑን፣ በአንቀጽ 9(3) ወይም (4) የተዘረዘሩት ማስረጃዎች ስለመኖራቸዉ መገለጽ ያለበት መሆኑን እና በቀጣይ መደበኛ የሆነ ጥያቄ እንደሚቀርብ መገለጽ እንዳለበት ተደንግጓል፡፡ ይህ ጥያቄ የደረሰዉ ሀገርም ወዲያዉኑ ምላሹን ማሳወቅ አለበት፡፡ መደበኛ ጥያቄዉም ተፈላጊዉ ከታሰረበት ቀን አንሰቶ በ 45( አርባ አምስት) ቀናት ዉስጥ ካደረሰዉ ጥያቄው የቀረበለት ሀገር ተፈላጊዉን መልቀቅ ይችላል፡፡ ነገር ግን የጊዜያዊ እስሩ መቋረጥ መደበኛ ጥያቄ ከቀረበ የተፈላጊዉን እንደገና ሜዝ እና የአሳልፎ መስጠት ሂደትን አያስቀርም፡፡
በስምምነቱ አንቀጽ 14 ላይ በተለያየ ወይም በተመሣሣይ ጉዳይ ከአንድ በላይ የአሳልፎ መስጠት ጥያቄ በተመሳሳይ ሰው ላይ ሲቀርብ በተጠያቂ ሀገር ጥያቄው ስለሚስተናገድበት አግባብ ሲያስቀምጥ ሁሉንም አግባብነት ያላቸዉ ሁኔታዎች በተለይም ጥያቄዉ ስምምነትን መሰረት አድርጎ የቀረበ ስለመሆኑ፣ የወንጀሉ ክብደት፣ ወንጀሉ የተፈፀመበት ጊዜና ቦታ፣ የተፈላጊው ግለሰብ እና የወንጀል ተጎጂ/ዎችን ዜግነት፣ ጥያቄዎቹ የቀረቡበትን ጊዜ እና ተላልፎ ከተሰተ
በኋላ ለሶስተኛ ወገን ተላልፎ የመሰጠት ዕድል ከግምት ውስጥ በማስገባት ወደየትኛው ሀገር ተላልፎ እንደሚሰጥ ለመወሰን የሚችል ስለመሆኑ ያስረዳል፡፡
በስምምነቱ አንቀጽ 15 መሠረት ተላልፎ የተሰጠ ግለሰብ ተላልፎ ከተሰጠበት ወንጀል ውጪ በሌላ የወንጀል ጉዳይ ምክንያት ሊያዝ፣ ሊከሰስ ወይም ሊታሰር እንደማይችል እንዲሁም ለሦስተኛ አገር ተላልፎ ሊሰጥ እንደማይችል ተደንግጓል። ሆኖም ግለሰቡ ከጠያቂ አገር ወጥቶ በፈቃደኝነት ወደዛው ሀገር ከተመለሰ፣ ግለሰቡ ነፃ ከተደረገ በኋላ ከሀገሪቱ መዉጣት እየቻለ በ
30 ቀናት ውስጥ ከጠያቂ አገር ካልወጣ ወይም ጠያቂ ሀገር ለተጠያቂ ሀገር በአንቀጽ 9 የተዘረዘሩትን ተገቢ የሆኑ ሰነዶችና መረጃዎችን በመሟላት የተጠያቂ አገርን ፈቃድ በመጠየቅ ተጠያቂ ሀገር ከተስማማች ከላይ የተቀመጠው ግዴታ ተፈጻሚ አይደረግም።
አንቀጽ 16 የሚደነግገዉ ተጠያቂ ሀገር ተፈላጊዉ ግለሰብ ተላልፎ እንዲሰጥ ከወሰነች በኋላ ግለሰቡ የሚተላለፍበትን ሂደት የሚያሳይ ሲሆን ግለሰቡ ተላልፎ በሚሰጥበት ጊዜ፣ ቦታ እና ሌሎች ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮች ላይ ሁለቱ ወገኖች በመመካከር መስማማት ላይ እንዲደርሱ የሚያስቀምጥ ሲሆን አሳልፎ የሚሰጠው አካል ተፈላጊው ግለሰብ ተላልፎ እንዲሰጥ በማሰብ ለምን ያህል ጊዜ በእስር ላይ እንደቆየ ለጠያቂው አካል የማሳወቅ ግዴታ እንዳለበትም ይደነግጋል፡፡ በዚህ መሠረት ጥያቄውን ያቀረበው አካል በተባለው ጊዜና ቦታ በመገኘት ግለሰቡን የመረከብ ግዴታ ያለበት ሲሆን ይህን ሳያደርግ ከቀረና ከተቆረጠው ጊዜ 30 ቀናት በላይ ካለፈ ግለሰቡን ሊለቅ እና ለወደፊት በዚሁ ግለሰብ ላይ በተመሳሳይ ጉዳይ ሚቀርብን የአሳልፎ የመስጠት ጥያቄውን ላለመቀበል እንደሚችል ተደንግጓል። ሆኖም ጥያቄውን ያቀረበው አካል ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት በተስማሙበት ጊዜ መረከብ የማይችልበት ሁኔታ ካጋጠመዉ ከሆነ ይህንኑ ወዲያዉኑ ለተጠያቂ ሀገር በማሳወቅ በድጋሚ በርክክቡ ሂደት ላይ ሊስማማ ይችላሉ፡፡
በስምምነቱ አንቀጽ 17 ተላልፎ እንዲሰጥ የተጠየቀው ግለሰብ ጥያቄው በቀረበለት አገር ተላልፎ እንዲሰጥ ከተወሰነ በኋላ ተላልፎ የሚሰጠዉ ሰዉ ላይ የአሳልፎ መስጠት ጥያቄ ከቀረበበት ጉዳይ ዉጭ ሌላ የወንጀል ምርመራ እተከናወነበት፣ ክስ ተመስርቶበት ወይም ቅጣት ተላልፎበት እስሩን በመፈፀም ላይ የሚገኝ ከሆነ የማስተላለፍ ሂደቱ በትብብር ተጠያቂ ሀገር ዉሳኔ ላልተወሰነ ጊዜ ሊዘገይ ወይም ሊቆይ ስለሚችልበት ሁኔታ በአንቀጹ (1) ተደንግጓል፡፡ በተጨማሪም በአማራጭነት የማስተላላፉ መዘግየት በጠያቂ ሀገር ህግ መሰረት ጉዳዩ በይርጋ የሚያልፍ ወይም
የምርመራዉን ሂደት የሚደናቅፍ ከሆነ በጠያቂው እና በተጠያቂው ሀገር መካከል በሚደረግ ስምምነት እና ቅድመ ሆኔታ መሰረት ተፈላጊውን በጊዜያዊነት ተላልፎ ሊሰጥ እንደሚችል ተደንግጓል። በተጨማሪም በሚተላለፈዉ ግለሰብ የጤና ሁኔታ አንፃር ተላልፎ ቢሰጥ ለህይወቱ የሚያሰጋ ሁኔታ ዉስጥ ካለ አግባብ ካለዉ የጤና ተቋም በጸደገፈ መረጃ ማሽጸላለፉ ሊራዘም ይችላል፡፡
በስምምነቱ አንቀጽ 18 መሠረት የአሳልፎ መስጠት ጥያቄ ያቀረበው ሀገር ተላልፎ የተሰጠው ግለሰብ ከፈጸመው የወንጀል ድርጊት የተገኘን ንብረት ወይም ወንጀሉን ለመፈፀም ጥቅም ላይ የዋሉ ንብረቶችን ወይም በፍርድ ሂደት እንደማስረጃ ሊያገለግሉ የሚችሉ ንብረቶች እንዲሰጡት ጥያቄ ያቀረበ እንደሆነ ጥያቄው የቀረበለት ወገን የሀገሩ ሕግ በሚፈቅድለት መሰረት ለሌላኛው አሳልፎ መስጠት አለበት፡፡ በተጨማሪም ተፈላጊዉ ግለሰብ በመሞቱ፣ በመጥፋቱ፣ በማምለጡ ወይም በሌላ ምክንያት ማስተላለፍ ባይቻል እንኳን ንብረቶቹ መመለስ አለባቸዉ፡፡ ሆኖም ንብረቶቹ በተጠየቀው አገር የተጀመረ ሌላ የወንጀል የፍርድ ሂደት የሚፈለጉ ከሆነ ንብረቶቹን ማስረከቡን ለሌላ ጊዜ ሊያስተላልፍ ወይም እንዲመለሱለት በሚያቀርበው በቅድመ ሁኔታ ጠያቂው አገር ከተስማማ ለጊዜው አሳልፎ ሊሰጥ እንደሚችል ተመልክቷል፡፡ የንብረቶቹ መሰጠት የሶስተኛ ወገኖችን ጥቅም እና መብት መንካት እንደሌለበት ተደንግጓል፡፡
በአንቀጽ 19 መሰረት ማንኛዉም የትብብር ጥያቄ እና ደጋፊ ሰነድ በትብብር ተጠያቂ ሀገር የስራ ቋንቋ ወይም በአንግሊዝኛ ትርጉም መቅረብ ያለበት መሆኑ ተደንግጓል፡፡
በስምምነቱ አንቀጽ 20 ላይ ከሌላ ሦስተኛ ሀገር ተላልፎ ለአንደኛው ወገን የተሰጠ ተፈላጊ በሌላኛው ግዛት ውስጥ እንዲተላለፍ የትብብር ጥያቄ ሲቀርብ ከአገራቱ ሕግ ጋር የማይቃረንና መሆኑን በማረጋገጥ ተፈላጊው እንዲያልፍ መፍቀድ እንዳለባቸው እና ጥያቄዉ እስከሚቀርብ ድረስ ለ 48 ሰዓታት የማቆየትግዴታ ለበት ሲሆን ሆኖም የመተላላፍ ሂደቱ በአዉሮፕላን ከሆነ እና አዉሮፕላኑ በጠያቂ ሀገር የግዛት ክልል ዉስጥ እንደሚያርፍ ቀድሞ ያልታቀደ ከሆነ ጥያቄ ማቅረብ አያስፈልግም፡፡
የስምምነቱ አንቀጽ 21 ከስምምነቱ አተገባበር ጋር ተያይዞ የሚመጡ ወጪዎችን የሚመለከት ሲሆን በዚህ መሠረት ጥያቄው የቀረበለት አካል አሳልፎ ከመስጠት ጥያቄው ጋር ተያይዞ በአገሩ የሚያወጣውን ወጪ፣ ተላልፎ የሚሰጠውን ግለሰብ በአገሩ ለመያዝ የሚያወጣውን ወጪ እና
ተላልፎ ከሚሰጠው ግለሰብ ጋር አብሮ ተይዞ ለሚተላለፍ ወንጀሉን ለመፈፀም ጥቅም ላይ የዋለ ንብረትን ለመያዝና ለማስተላለፍ የሚያወጣውን ወጪ እንደሚሸፍን ተደንግጓል። ጥያቄውን ያቀረበው ሀገር በበኩሉ ተላልፎ የሚሰጠውን ግለሰብ እና ንብረት ወደ አገሩ ለማጓጓዝ የሚያስፈልገውን ወጪ እንደሚሸፍን ተደንግጓል።
አንቀጽ 22 ደግሞ በስምምነቱ አፈፃፀምም ሆነ አተረጓጎም ላይ በሁለቱም ሀገራት ማዕከላዊ ባለስልጣናት የሚነሱ አለመግባባቶች በዲፕሎማሲያዊ መስመር በሚደረግ ምክክር እንደሚፈቱ ይደነግጋል፡፡
አንቀጽ 23 ስምምነቱ ሁለቱም ሀገራት በሌላ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የሚያገኙትን ማንኛዉንም መብት ሆነ የተጣለባቸዉን ግዴታ ሊያቀር የማይችል መሆኑን ሲደነግግ የስምምነቱ አንቀጽ 24 የመጨረሻ ድንጋጌዎችን የያዘ ሲሆን ስምምነቱ ወደ ሥራ የሚገባው በሁለቱም ሀገራት መጽደቁን በሚመለከት ሰነድ በዲፕሎማቲክ መስመር የመጨረሻዉ ልውውጥ ከተደረገበት ከ30 ቀናት በኋላ እንደሆነ ተደንግጓል። ስምምነቱ በሀገራቱ የጋራ ፈቃድ ላይ ተመስርቶ መሻሸል እንደሚችል፤ተፈፃሚነቱ ስምምነቱ ከመፈረሙ በፊት ለተፈፀሙ ወንጀሎችም መሆን እንዳለበት፣ በተጨማሪም ሀገራቱ የ180 ቀናት የጽሑፍ ቅድመ-ማስታወቂያ በመስጠት የስምምነቱን ተፈጻሚነት ቀሪ ማድረግ እንደሚችሉ ተደንግጓል። ይህም ቀድሞ የተጀመሩ የአሳልፎ መስጠት ሂደቶች ላይ የሚስከትለዉ ተጽዕኖ የሌለ መሆኑ ተደንግጓል፡፡ በመጨረሻም ስምምነቱ ወደ ስራ ከገባበት ጊዜ በፊት የተፈፀሙ ወንጀሎችን ጨምሮ በሀገራቱ በሚቀርቡ ማንኛዉም የአሳልፎ መስጠት ጥያቄዎች ላይ ተፈፃሚ እንደሚደረጉ ተደንግገዋል፡፡
6. ማጠቃለያ
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ኢትዮጵያ ያላቸዉ ግንኙነት ለረጅም ጊዜ የነበረ እና በተለይም ደግሞ በአሁኑ ሰዓት ዘርፈ ብዙ እና ከዕለት ወደ ዕለት እያደገ ያለ በተለይም በ ንግድ እና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ያላቸዉ ግንኙነት እየጨመረ የመጣ በመሆኑ እና በዚህም ምክንያት ኢትጵያውያን በቀላሉ ወደ ተባበሩት የአረብ ኤምሬቶች መጓዝ መቻላቸው ወንጀለኞችም ይህንን ሁኔታ በመጠቀም ከሕግ ለማምለጥ ወደ ተባበሩት የአረብ ኤምሬቶች ለመሄድ የሚችሉበት አጋጣሚ ሰፊ በመሆኑ በወንጀል ጉዳይ ግለሰቦችን አሳልፎ መስጠትን አስመልክቶ የተደረገው ስምምነት በሁለቱ አገሮች ሰላምን፣ ፀጥታን እና መረጋጋትን ለማረጋገጥ አስተዋፅኦ የሚያደርግ
የትብብር ማዕቀፍን የሚፈጥር በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ እንደሚሆን ይታመናል። ማንኛውም ወንጀልን የፈጸመ ግለሰብ ለፍትሕ መቅረብ ያለበት በመሆኑና ወንጀልን ፈጽሞ ወደሌላ አገር በመሸሸጉ ከተጠያቂነት ሊያመልጥ የማይገባ ስለሆነ አሳልፎ የመስጠት ስምምነቱን ተግባራዊ ማድረጉ ጠቃሚ እንደሚሆን ይታመናል። ከዚህ አንጻር በሚኒስትሮች ምክር ቤት እና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውይይት ተደርጎበት እንዲጸድቅ ረቂቅ አዋጁን አያይዘን አቅርበናል።
አዋጅ ቁጥር /2015
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት እና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መንግስት መካከል የተደረገውን የአሳልፎ መስጠት ስምምነት ለማጽደቅ የወጣ አዋጅ
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት እና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መንግስት መካከል እ.ኤ.አ. መስከረም 21 ቀን 2022 በአቡዳቢ የተፈረመ በመሆኑ፤
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 55 ንዑስ አንቀጽ (1) እና
(12) መሠረት የሚከተለው ታውጇል፡፡
1. አጭር ርዕስ
ይህ አዋጅ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት እና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መንግስት መካከል የተደረገውን የአሳልፎ መስጠት ስምምነት ማጽደቂያ አዋጅ ቁጥር..../2015” ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡
2. ስምምነቱ ስለመጽደቁ
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት እና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መንግስት መካከል እ.ኤ.አ. መስከረም 21 ቀን 2022 በአቡዳቢ የተፈረመው የአሳልፎ መስጠት ስምምነት ፀድቋል፡፡
3. የኢፌዲሪ ፍትህ ሚኒስቴር ኃላፊነት
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ይህን ስምምነት ለማስፈጸም አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎችን ሁሉ እንዲወስድ በዚህ አዋጅ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡
4. አዋጁ የሚፀናበት ጊዜ
ይህ አዋጅ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ የፀና ይሆናል:: አዲስ አበባ…………... ቀን 2015 ዓ.ም.
ሳህለወርቅ ዘዉዴ
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት
Proclamation No /2022
A PROCLAMATION TO RATIFY THE EXTRADITION TREATY BETWEEN THE GOVERNMENT OF THE FEDERAL DEMOCRATIC REPUBLIC OF ETHIOPIA AND THE GOVERNMENT OF THE UNITED ARAB EMIRATES
WHEREAS the Extradition Treaty between the Government of the Federal Democratic Republic of Ethiopia and the Government of the United Arab Emirates has been signed in Abu Dhabi , on the 21st September, 2022;
NOW, THEREFORE, in accordance with sub-articles (1) and (12) of Article 55 the Constitution of the Federal Democratic Republic of Ethiopia, it is hereby proclaimed as follows:
1. Short Title
This Proclamation may be cited as the “Extradition Treaty between the Government of the Federal Democratic Republic of Ethiopia and the Government of the United Arab Emirates Ratification Proclamation No.…/2022”.
2. Ratification of the Agreement
The Extradition Treaty signed in Abu Dhabi on the 21st of September 2022 between the Government of the Federal Democratic Republic of Ethiopia and the Government of the United Arab Emirates, is hereby ratified.
3. Responsibility of the FDRE Ministry of Justice
The FDRE Ministry of Justice is hereby empowered to undertake all acts necessary for the implementation of the Treaty.
4. Effective Date
This Proclamation shall come into force on the date of its publication in the Federal Negarit Gazeta.
Done at Addis Ababa on this ….day of the month of n the Year 2022
Sahilework Xxxxxx
PRESIDENT OF THE FEDERAL DEMOCRATIC REPUBLIC OF ETHIOPIA