መደረጉን የበታች ፍ/ቤቶች ውሣኔ በግልጽ ያሳያል፡፡ ይሁን እንጂ የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2089/2/ ድንጋጌ በድንጋጌው ንዑስ ቁጥር አንድ ስር የተቀመጠውን መርህ በልዩ ሁኔታ ያስቀመጠ ሲሆን ባለሃብቱ ወይም ጠባቂው ጥፋት ማድረጋቸው ከተረጋገጠ ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑን ድንጋጌው ያሳያል፡፡ በዚህ ልዩ ሁኔታ አነጋገር መሰረት የመኪናውን ባለሃብት ወይም ጠባቂውን ጥቅም በሌለው ግንኙነት መኖሩ ቢረጋገጥም...
ታህሣስ 15 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች፡- አልማው ወሌ
ዓሊ መሐመድ ረታ ቶሎሣ አዳነ ንጉሴ
ሙስጠፋ አሕመድ
አመልካች፡- 1. የኢ.ፌ.ዲ.ፌዴሬሽን ምክር ቤት ነ/ፈጅ ጥሩነሽ ገረመው ቀረቡ
2. አቶ ተስፋዬ ጌታሁን ተጠሪ፡- ቄስ ማሞ ይታፈሩ ቀረቡ
መዝገቡን ተመርምሮ የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡ ፍ ር ድ
ጉዳዩ ምንም የጥቅም ግንኙነት በሌለበት ሁኔታ አቅመ አዳም ያልደረሰን ሕፃን በተሽከርካሪ ጭኖ በመጓዝ ሂደት ተሽከርካሪው ተገልብጦ ሕፃኑ ለሞት ሲዳረግ የመኪናውን ባለንብረትና አሽከርካሪው ስላለባቸው ፍትሐብሔር ኃላፊነት የሚመለከት ነው፡፡
ክርክሩ በመጀመሪያ የተታየው በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ነው፡፡ በሥር ፍርድ ቤት አመልካቾች ተከሣሽ፣ ተጠሪ ደግሞ ከሣሸ በመሆን ተከራክረዋል፡፡ ተጠሪ 2ኛ አመልካች አሽከርካሪ በመሆን የ1ኛ አመልካች ንብረት የሆነውን የሰሌዳ ቁጥር 4-14199 ኢት ፒካፕ የሆነ መኪና ሲያሽከረክር ግንቦት 08 ቀን 2002 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ የካ ክፍል ከተማ ቀበሌ 03/04 ብረት ድልድይ ከተባለ ቦታ ወደ ፈረንሣይ ኢንባሲ አቅጣጫ እያሽከረከረ በውጪ እቃ መጫኛ ላይ እድሜው 13 አመት የሆነ ደረጃ ማሞ የተባለ ህፃን ጭኖ በመጓዝ ላይ እያለ ሕፃኑ ወድቆ እንዲሞት ማድረጉ ሕፃኑን በሕይወት እያለ ጫማ በመጥረግ ለተጠሪ ገቢ ሲያገኙላቸው የነበረ መሆኑን በጉዳቱ ምክንያት ለህክምናም ሆነ ለቅብር ስነ ስርዓት ወጪ ያወጡ መሆኑን፣ ሕፃኑ በሕይወት ቢኖሩ ኑሮ እድሜው ሃምሳ ዓመት እስኪሞላው ለተጠሪ ያስገኝ የነበረው የቀን ገቢ ብር 8.00 እንደሚቀጥልና በመሞቱ ምክንያት ግን መቋረጡን ዘርዝረው ይህንኑ ገቢና በጉዳቱ ምክንያት ያወጡትን ወጪ በድምሩ ብር 119,870.00 (አንድ መቶ አስራ ዘጠኝ ሺህ ስምንት መቶ ሰባ ብር) እንዲከፍሉ እንዲወሰንላቸው ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡ የአሁኑ አመልካችም ለክሱ ኃላፊነት የሌለባቸው መሆኑንና የቀረበው የካሳ ክፍያም የሕግ መሰረት የሌለው መሆኑን
ጠቅሰው ተከራክረዋል፡፡ እንዲሁም የኢትዮጵያ መድን ድርጅትም በጉዳዩ ላይ ጣልቃ ገብቶ እንዲከራከር ተደርጓል፡፡
የሥር ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክርና የተጠሪን ምስክሮች በመስማት ጉዳዩን መርምሮ አመልካቾችን ለክሱ ኃላፊ ያደረጋቸው ሲሆን ጣልቃ ገቡን ግን ከክሱ ነፃ እንዲሰናበት ወስኗል፡፡ የካሳውን መጠን በተመለከተም በርትዕ በድምሩ ብር 31,300.00 (ሰላሳ አንድ ሺህ ሶስት መቶ ብር) እንዲሆን ወስኗል፡፡ በዚህ ውሳኔ አመልካቾች ቅር በመሰኘት ይግባኛቸውን ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርበው ይግባኙ በፍ/ስ/ስ/ሕግ ቁጥር 337 ተሰርዞባቸዋል፡፡ የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ሲሆን ጉዳዩ ለሰበር ችሎት እንዲቀርብ በመደረጉ ተጠሪ ቀርበው ግራ ቀኙ በፅሁፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል፡፡
የጉዳዩ አመጣጥና በሰበር የቀረበው ክርክር ከላይ ባጭሩ የተገለፀው ሲሆን እኛም ጉዳዩን አመልካቾች ለጉዳቱ ኃላፊ ናቸው ተብሎ የተሰጠው ውሳኔ በአግባቡ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል፡፡
በክርክሩ ውስጥ በፍሬ ነገር ደረጃ የተረጋገጡት ነጥቦች የተጠሪ ልጅ የሕዝብ ማመላለሻ ባልሆነው የ1ኛ አመልካች መኪና በ2ኛ አመልካች በእቃ መጫኛው ላይ ተሳፍሮ ሲሄድ ወድቆ ለሕልፈተ ሕይወት መዳረጉና 2ኛ አመልካች የ1ኛ አመልካች ተቀጣሪ ሰራተኛ መሆናቸው፣ ለጉዳቱ መድረስ ጥፋቱ የሹፌር መሆኑን የሚያሳዩ ናቸው፡፡
ወደ ሕጉ ስንመጣ በመሰረቱ የፍ/ብ/ሕግ ቁ. 2089/1/ የሚገኘው ከውል ውጪ ስለሚደርስ አላፊነትና ያለአግባብ ስለመበልፀግ በሚለው በፍታብሔር ሕጉ በአንቀጽ 13 ስር ነው፡፡ ተጠሪ አመልካቾች የከሰሱትም ከውል ውጪ ደረሰ የሚለውን ኃላፊነት መሰረት በማድረግ ነው፡፡ በስር ፍ/ቤቶች በተደረገው ክርክር በፍሬ ነገር ረገድ እንደተረጋገጠው ህፃኑ የተባለው ጉዳት የደረሰበት በ1ኛ አመልካች መኪና በመገጨቱ ሳይሆን፣ በመኪናው ላይ በ2ኛ አመልካች እውቅና ተሳፍሮ ሲሄድ ከመኪናው በመውደቁ ምክንያት ነው፡፡ በእርግጥ መኪናው የ1ኛ አመልካች ንብረት ነው፡፡ ሆኖም መኪናው ገንዘብ በማስከፈል ሰዎችን የሚያጓጉዝ የንግድ መኪና ሳይሆን ለመንግስት ስራ ጥቅም ላይ የሚውል ነው፡፡ ይህ በመሆኑም ህፃኑ በመኪናው ላይ ስለመሳፈሩ 1ኛ አመልካች ያውቃል ወይም ማወቅ ይጠበቅበታል ተብሎ አይገመትም፡፡ መኪናው የተሰማራው ሰዎችን ለማጓጓዝ ባለመሆኑ 1ኛ አመልካች ሟቹን ህፃን በማሳፈር ያገኘው ጥቅም አለ ብሎ ለመደመደም የሚቻልበት ሕጋዊ ምክንያት የለም፡፡ በፍሬ ነገር ረገድ እነዚህን ሁኔታዎች ከተረጋገጡ ቀጥሎ መታየት ያለበት አመልካቾች ለደረሰው ጉዳት ኃላፊ የሚሆኑበት የሕግ አግባብ አለ? ወይስ የለም? የሚለው ነው፡፡
በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2081/1/ እንደተደነገገው የመኪናው ባለቤት መኪናው በሶስተኛ ወገን ላይ ለሚያደርሰው ጉዳት ኃላፊ የሚሆንበት አግባብ አለ፡፡ ይህ እንግዲህ በአጠቃላይ የተቀመጠ የኃላፊነት መርህ ሲሆን፣ በቁ 2089 ደግሞ ልዩ ሁኔታ ማለትም የመኪናው ባለቤት ኃላፊ የማይሆንበት ሁኔታ ተደንግጎአል፡፡ ከድንጋጌው ርእስ መገንዘብ እንደሚቻለው ጉዳቱ የደረሰው ጥቅም በሌለው ግንኙነት ጊዜ ሲሆን የመኪናው ወይም ጉደቱን ያደረሰው ንብረት ባለቤት ኃላፊነት አይኖርበትም፡፡ ከላይ እንዳመለከትነው ተጠሪ በአመልካች መኪና የተገለገለው ለአመልካች ጥቅም በማያስገኝ ሁኔታ ነው፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ 1ኛ አመልካች በዚህ ረገድ ጥፋት ፈጽሞአል አልተባለም፡፡ ይልቁንም የ1ኛ አመልካች ሹፌር፤ 2ኛ አመልካች ጥፋት መፈፀሙ ተረጋግጧል ተብሎ 1ኛ አመልካች ኃላፊነቱን እንዲወስድ
መደረጉን የበታች ፍ/ቤቶች ውሣኔ በግልጽ ያሳያል፡፡ ይሁን እንጂ የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2089/2/ ድንጋጌ በድንጋጌው ንዑስ ቁጥር አንድ ስር የተቀመጠውን መርህ በልዩ ሁኔታ ያስቀመጠ ሲሆን ባለሃብቱ ወይም ጠባቂው ጥፋት ማድረጋቸው ከተረጋገጠ ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑን ድንጋጌው ያሳያል፡፡ በዚህ ልዩ ሁኔታ አነጋገር መሰረት የመኪናውን ባለሃብት ወይም ጠባቂውን ጥቅም በሌለው ግንኙነት መኖሩ ቢረጋገጥም ተጠያቂ ማድረግ የሚቻለው ባለሃብቱ ወይም ጠባቂው ጥፋት ካለባቸው ብቻ ነው፡፡ በድንጋጌው ስር ባለሃብት የሚለው ቃል ግልጽ ሲሆን ጠባቂ የሚለው ቃል ግን ግልጽነት የጎደለው መሆኑ የሚታመን ነው፡፡ በዚህ ረገድ በተጠሪ በኩል ለቃሉ እየቀረበ ያለው ክርክር ባይኖርም ተቀጣሪ ሹፌር ጠባቂ በሚለው ቃል የሚሸፈን ነው ወይስ አይደለም የሚለው የሕግ ጥያቄን ማየቱ ተገቢ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የአማርኛው አቻ የእግሊዘኛ ቃሉ ‘’holder’’ በሚል የተቀመጠ ሲሆን ይህ ቃል በሕግ መዝገበ ቃላት ከተሰጠው ትርጉም አንዱ a person who possesses or uses property በሚል የተቀመጠ መሆኑን ታዋቂው የብላክስ ሎው መዝገበ ቃላት ያሳያል፡፡ ከዚህም መገንዘብ የሚቻለው ጠባቂ የሚለው ቃል ለራሱ ጥቅም መኪናውን ይዞ የሚገኘውን ሰው መሆኑን ነው፡፡ ሹፌር በሰራው ምክንያት ላጠፋው ጥፋት ካልሆነ በስተቀር አሰሪው የመንግስት መስሪያ ቤት ወይም ባለሃብት ተጠያቂ የሚሆንበት አግባብ የሌለ መሆኑን ተጠቃሹን ድንጋጌው ከፍ/ህ/ቁጥር 2126/2/፣2127፣2130 እና ከፍ/ሕ/ቁጥር 2131 ድንጋጌዎች ይዘት ጋር በማገናዘብ ስናነብ የምረዳው ጉዳይ ነው፡፡ የ1ኛ አመልካች ሹፌር የሆኑት 2ኛ አመልካች ስራውን ሲሰሩ የፈፀሙት ጥፋት የሌለ ስለመሆኑ ወይም ጥፋቱ የ2ኛ አመልካች የግላቸው ስለመሆኑ 1ኛ አመልካች በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2126/2/ እና 2127 ድንጋጌዎች አግባብ የማስረዳት ግዴታውን አልተወጣም፡፡ ይልቁንም ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግላቸው ከሚገባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል የሆነውን የተጠሪ ልጅ ህፃን ደረጀ ማሞን በእቃ መጫኛው ላይ 2ኛ አመልካች በስራ ላይ እያሉ ጭነው ለህልፈት መዳረጋቸው በፍሬ ነገር ደረጃ ተረጋግጧል፡፡ አንድ ባለሃብት ጥቅም በሌለው ግንኙነት ለደረሰ ጉዳት ኃላፊነት የሚወስድበት ሕጋዊ አግባብ የሌለ መሆኑን ይህ ችሎት በሰ/መ/ቁጥር 38457 እና በሌሎች በርካታ መዛግብት በአዋጅ ቁጥር 454/1997 አንቀጽ 2/1/ በየትኛውም እርከን የሚገኝ ፍ/ቤትን የሚያስገድድ የህግ ትርጉም የሰጠበት ጉዳይ ቢሆንም ይህ ጉዳይ ግን ከጉዳዩ ልዩ ባህርይ ሊታይ የሚገባው ስለመሆኑ በክርክሩ ሂደት የተረጋገጡት ፍሬ ነገሮች የሚያስገነዝቡን ጉዳይ ሁኖ አግኝተናል፡፡ በመሆኑም በሰ/መ/ቁጥር 38457 የተሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም በመሰረታዊ ፍሬ ነገሮች በዚህ መዝገብ ከተያዘው ጉዳይ ጋር የሚገኛኝ ሁኖ ስላልተገኘ ለውሳኔው መሰረት ለማድረግ የምንገደድበት ሁኖ አልተገኘም ምክያቱም ጉዳቱ የደረሰው ህፃን ላይ ከመሆኑም በላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግለት ለሚገባው ለዚህ ህፃን 2ኛ አመልካች በ1ኛ አመልካች ስራ ላይ እንዳሉ ባሉበትና ጥንቃቄ ሳያደርጉ በተሸከርካሪ እቃ መጫኛ ጭነው ሲጓዙ ለህልፈት የዳረጉት ስለመሆኑ በፍሬ ነገር ደረጃ የተረጋገጠ በመሆኑ በሰ/መ/ቁጥር 38457 የተሰጠው አስገዳጅ የህግ ትርጉም በዚህ መዝገብ ከተያዘው ጉዳይ ጋር ሲነፃፀር ከተበዳዩም ሆነ በተበዳዩና በባለንብረቱ ከነበረው ግንኙነት ጋር የሚገናኝ አይደለምና ህፃናት በኢ.ፊ.ዲ/ሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 36/2/፣15 እና 25 ድንጋጌዎች እንዲሁም ኢትዮጵያ ተቀብላ ባፀደቀቻቸው አለም አቀፍ ስምምነቶም በሕፃናት መብቶች ስምምነት አንቀጽ 3፣ 6/1/ በአፍሪካ ህፃናት መብቶችና ደህንነት ቻርተር አንቀጽ 4/1/፣5/1/ ድንጋጌዎች በሕይወት የመኖርና የአካል ደህነት ጥበቃ የተደረገላቸው መሆኑ ግልጽ ስለሆነ የካሳ ክፍያ ጉዳይም እነዚህን ሕጎችን ሁሉ እግምት ውስጥ ማስገባት ያለበት ነው በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች አመልካቾች በተጠሪ ላይ ለደረሰው ጉዳት ኃላፊ የማይሆኑበት
አግባብ የለም ሲጠቃለልም የሰር ፍ/ቤቶች በጉዳዩ ላይ የሰጡት ውሳኔ በውጤት ደረጃ ሲታይ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ነው ለማለት የሚቻል ሁኖ ስላላገኘነው ተከታዩን ወስነናል፡፡
ው ሳ ኔ
1. በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በመ/ቁ 37334 ሰኔ 17 ቀን 2005 ተሰጥቶ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 140091 ሐምሌ 11 ቀን 2005 ዓ/ም የፀናው ውሳኔ በፍ/ብሕ/ስ/ስ/ህ/ቁ 348/1/ መሰረት ጸንቷል
2. አመልካቾች በተጠሪ ልጅ ላይ ደረሰ ለተባለው የሞት ጉዳት ኃላፊነት አለባቸው ተብሎ በድምሩ ብር 31,300.00 /ሰላሳ አንድ ሺህ ሶስት መቶ ብር/ ለተጠሪ ሊከፍሉ ይገባል ተብሎ መወሰኑ ባግባቡ ነው ብለናል
3. በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ በሚመለከት ግራ ቀኙ ወገኖች የየራሳቸውን ይቻሉ
ት ዕ ዛ ዝ
ሐምሌ 22 ቀን 2005 ዓ/ም ተሰጥቶ የነበረው እግድ ተነስቷል፡፡ ለሚመለከታቸው አካላት ይፃፍ፡፡
መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡
የማይነበብ የአራት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡
የመስማሚያ ሀሳብ
እኔ ስሜ በሁለተኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሰው ዳኛ አብላጫው ድምፅ አመልካች ለተጠሪ ካሳ መክፈል ኃላፊነት አለበት በማለት ደረሰበት ድምዳሜ ሙሉ በሙሉ እስማማለሁ፡፡ ሆኖም አብላቻው ድምፅ በሌሎች መዝገቦችና ተሳፋሪዎች ካሳ ሊያገኙ አይገባም በማለት በሰጣቸው የህግ ትርጉሞች የማልስማማ በመሆኑ የመኪናው ባለሀብት ሰራተኛው ላጠፋው ጥፋት ተጠያቂ በመሆኑ በፍትሐብሔር ህግ ቁጥር 2089 ንዑስ አንቀፅ 2 ድንጋጌ መሰረት ካሳ የመክፈል ኃላፊነት አለበት በማለት የመስማሚያ ሀሳቤን አስፍሬአለሁ፡፡
ቤ/ዮ
የማይነበብ የአንድ ዳኛ ፊርማ አለበት፡፡