የስምምነቱ መጽደቅ ለአገራችን የሚኖረዉ ጠቀሜታ. ሀገራችን እየተገበረች ያለችዉን የልማት እና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አጠናክሮ ለማስቀጠል ጉልህ ሚና ከሚጫወቱ ነገሮች መካከል የሕግ የበላይነት መከበር ነው፡፡ የዚህም አንዱ መገለጫ የተለያዩ የወንጀል መረጃዎች/ማስረጃዎች በመለዋወጥ ወንጀለኞች ከቅጣት የማያመልጡበትን ሁኔታ መፍጠር ሲሆን ይህንንም ለማከናወን በእንካ ለእንካ (Principle of Reciprocity) ከሚካሄዱ ትብብሮች ባለፈ በሀገራት መካከል ስምምነቶችን መፈራረም እና ፀድቀው ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረግ ዋናው መሳሪያ ነው፡፡ የተባበሩት የአረብ ኤምሬቶች እና ኢትዮጵያ ያላቸዉ ግንኙነት ለረጅም ጊዜ የነበረ እና በተለይም ደግሞ በአሁኑ ሰዓት ዘርፈ ብዙ እና ከዕለት ወደ ዕለት እያደገ መምጣቱ ይታወቃል፡፡ በተለይም በንግድ እና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ያላቸዉ ግንኙነት እየጨመረ የመጣ በመሆኑ እና በዚህም ምክንያት ኢትጵያውያን በቀላሉ ወደ ተባበሩት የአረብ ኤምሬቶች መጓዝ ለወንጀል ክስ፣ ምርመራ እና ክስ ሂደት የሚያስፈልጉ መረጃ እና ማስረጃዎች እንዲሁም ለወንጀል መፈፀሚያነት የዋሉ፣ ሊዉሉ የታሰቡ ወይም የወንጀል ፍሬ የሆኑ ንብረቶች ሊሸሹ የሚችሉበት ዕድል ከፍተኛ ነዉ፡፡ በመሆኑም እነዚህን ጉዳዮች በተመለከተ ለሚደረጉ ትብብሮች በሕግ ማዕቀፍ ምላሽ ለማሰጠት ስምምነቱ አስፈላጊ ነዉ፡፡